መስከረም 27/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ሕግ እና ሥርዓት በማያከብሩ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ የታክሲ አሽከርካሪዎች አማካኝነት ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ እንድንከፍል በመገደዳችን ለአላስፈላጊ ወጪ ተዳርገናል ሲሉ ቅሬታቸውን ለአሐዱ አቅርበዋል።

ነዋሪዎቹ በቅሬታቸው ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ ከማስከፈል በተጨማሪ፤ ማመናጨቅ፣ መንገድ ላይ ማውረድ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የሚታይ ሥርዓት አልበኝነት እና የሥነ ምግባር ጉድለት እንደሚያስተናግዱ አብራርተዋል።

በዚህም ሳቢያ ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን የገለጹም ሲሆን፤ መሰል ሕገ-ወጥነት በከተማዋ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ እየተባባሰ መምጣቱን አስረድተዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎት በሚጠቀሙበት ወቅት፤ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ ትርፍ መጫን እና ተሸከርካሪዎችን በመጠቀም የሚደረጉ ስርቆቶች በዋናነት የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች እንደሆኑም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የተሳፋሪን መብት አለማክበር፣ ያለታርጋ ማሽከርከር እና ሌሎችም የትራፊክ ሕግ ጥሰቶች ለከፋ ችግርና እንግልት እየዳረጋቸው መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል።

አሐዱም የነዋሪዎችን አቤቱታ በመያዝ፤ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮን ጠይቋል።

በቢሮ የትራንስፖርት አገልግሎት ክትትል ዳይሬክተር ጌትነት ታመነ በሰጡት ምላሽ፤ በሩብ በጀት ዓመቱ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ ትርፍ መጫን፣ ተሳፋሪውን ማንገላታትና መሰል ሕገ-ወጥ ተግባራትን በፈፀሙ 911 የከተማ ታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ በተወሰደ ሕጋዊ እርምጃ ከ990 ሺሕ ብር በላይ የቅጣት ገንዘብ መሠብሰቡን ለአሐዱ ተናግረዋል።

እርምጃ የተወሰደባቸው ሌሎች አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና ትርፍ መጫን ላይ ተሰማርተው እንደነበርም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

ሕግ እና ሥርዓት አክብረው የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ ተሳፋሪውን የሚያጉላሉ በርካቶች መሆናቸውን ያወሱት ዳይሬክተሩ፤ ተሳፋሪዎች መሰል ችግሮች አጋጥሟቸው ጥቆማ በማድረጋቸው ምክንያት እርምጃዎቹ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያነሷቸውና ሌሎችም የትራፊክ ሕግ ጥሰቶች ማህበረሰቡን ለከፋ ችግርና እንግልት እየዳረጉ መሆኑን ያመኑት ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይም እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለማረም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በከተማዋ ትርፍ መጫንና ከታሪፍ በላይ ማስከፈል በሰፊው የሚስተዋል በመሆኑ፤ ማህበረሰቡ ለአላስፈላጊ ወጪና ለትራፊክ አደጋ እንዳይጋለጥ እነዚህ ከተፈቀደው ውጪ የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ለትራፊክ ደህነት አካላት በማጋለጥ ሕብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ የከተማ ታክሲ አሽከርካሪዎች አማካኝነት ለአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት ተዳርገናል በማለት በተደጋጋሚ አቤቱታቸውን ሲያሰሙ ይደመጣል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ