ሰኔ 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ከሁለት ዓመት በላይ የቀጠለው ግጭትን የማንነትና የወሰን ጥያቄ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ሲል የሰላም ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚኒስትር አማካሪ የሆኑት ካይዳኽ ገዛኸኝ ለአሐዱ እንደተናገሩት ከሆነ፤ በክልሉ ያሉ ወጣቶችን አስቆጥቶ ወደ ግጭት ያስገባው የማንነትና የወሰን ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የደህንነትና የሕገ መንግስት ይሻሻል ጥያቄዎች ከክልሉ ሲነሱ በመቆየታቸው ነው።
"የአማራ ክልል ምሁራኖች በቡድንም ሆነ በተናጥል የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ ማንሳት ከጀመሩ ውለዉ አድረዋል" ያሉት አማካሪዉ፤ እነዚህ ጥያቄዎች በአፋጣኝ ባለመመለሳቸው አሁን ላይ በክልሉ የሚስተዋለው ግጭት ለመቀስቀሱ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በክልሉ የሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎች በሌሎች ክልሎችም እንደሚነሱ ገለጸው፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊን ከሚያነሷቸዉ ጥያቄዎች ጋር በጋራ እንደሚፈቱ አፅንኦት ሰጥተዋል።

አሐዱም "ሰላም ሚኒስቴር እንደ ተቋም በሀገሪቱ ላይ ሰላም እንዲሰፍን ምን ያህል በመንግሥት ላይ ጫና መፍጠር እየቻለ ነው? ሲል ጠይቋል።
አማካሪው በሰጡት ምላሽ፤ "ተቋሙ መንግሥት ያቋቋመው እንደመሆኑ፤ አስታራቂ ሊሆን አይችልም" ሲሉ አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
"ነገር ግን ሕግና ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በሀገሪቱ የሚታዩ ግጭቶች በንግግር እና በውይይት እንዲፈቱ ሚኒስቴሩ የማማከር ሥራውን አጠናክሯ ይቀጥላል" ሲሉ ለአሐዱ አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ