መስከረም 27/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ በቀዳሚነት የፈረመችው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት (AfCFTA) ድርድርን ማጠናቀቋን ተከትሎ፤ መስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሸቀጦች ዘርፍ የንግድ ትግበራ በይፋ እንደምትጀምር የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
የንግድ ትስስርና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ያስሚን ውሀብረቢ እንደገለጹ፤ የመጀመርያው የንግድ ልውውጥ በምስራቅና በደቡብ አፍሪካ አገራት ላይ ትኩረት ያደርጋል።

በማስጀመሪያ ንግዱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ ሥጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በየብስ ትራንፖርት ቡና፣ የጥራጥሬ ምርቶችና የቅባት እህሎች ወደ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ወደ ደቡብ አፍሪካ ይላካል፡፡
አህጉራዊ ነፃ ንግድ ስምምነቱ ትግበራ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ለሀገራችን ንግድ ተወዳዳሪነትና ኢንቨስትመንትን ያነቃቃል፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ ለሸማቹ ህብረተሰብ የተሻለ አማራጭ የምርት አቅርቦት ያስገኛል ሲሉም አስረድተዋል።
በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ፣ በአፍሪካ ሀገራት መካከል የገበያ ትስስርን ለማስፈት የሚያስችል እና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ የንግድ ሥርዓት ትግበራ ውጤታማ እንዲሆን መንግሥትና ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሯቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ ወ/ሮ ያስሚነን ገልጸው፤ ምርቶችን በጥራት እና በብዛት ማቅረብ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የትራንስፖርትና የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትን ማጠናከር እንዲሁም የጉምሩክ ሂደቶችን ማዘመን እና "የጥራት መንደርን" በመጠቀም የምርቶችን ጥራት ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በንግድ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ሴክሬታሪያት ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶችና አምባሳደሮች፣ እንዲሁም ላኪዎችና አምራቾች ይሳተፋሉ ተብሏል።
በመርሃ ግብሩ ምርት የመላክ ሥነ-ሥርዓት፣ የፓናል ውይይት እና በድርድር ሂደቱ ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው ተቋማትና ግለሰቦች ዕውቅና የመስጠት መርሐ-ግብር መያዙን አሐዱ ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ