መስከረም 27/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚስተዋሉ አለመግባባት እና ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት በገለልተኛ አካል ሰላማዊ ድርድሮችን ማጠናከር እንደሚገባው አሐዱ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ገልጸዋል፡፡

የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ በትላንትናው ዕለት በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሰላማዊ መንገድ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በዚህም "ምንም እንኳ በየጊዜው የሚስተዋሉ የኃይል እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም መንግሥት ሙሉ ዝግጁነትና ዘመናዊ አቅም ቢኖረውም፤ የዛሬውን ግጭት በማሸነፍ ለነገው ትውልድ ቂምና ቁርሾ አናወርስም የሚል መርህ በመከተል በዛሬ ብልሃትና ትዕግስት ለነገ ሰላም ዘላቂ ሰላም የሚበጅ አካሄድን መርጧል" ሲሉ ተናግረዋል።

አሐዱ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የሚስተዋለውን ግጭት በዘላቂነት ለመፋታት መንግሥት አሁንም የተጠናከረ ሥራ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

መንግሥት በተለያየ ጊዜ ድርድሮችንና የሰላም አማራጮችን መከተሉን እንደሚያነሳ የገለጹት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስሀቅ ወልዳይ ናቸው።

ነገር ግን አሁንም ድረስ በሀገሪቱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በስፋት የሚስተዋሉ በመሆኑ፤ እውነተኛ ሰላምን ሊያረጋግጥ የሚችል ድርድር መከተል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለዚህም ደግሞ በተለይም ገለልተኛ በሆነ አካል የድርድር መርሆችን በመከተል ለጋራና ዘላቂ ሰላም ለመስራት የበለጠ ቁርጠኛ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር በበኩላቸው፤ መሬት ላይ የወረደና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት መንግሥት ግልፅ በሆነ መንገድ መሥራት እንደሚጠበቅበት ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

በየቦታው በሚታዩ ግጭቶች ሳቢያ በርካታ ልማቶች በሚፈለገው ልክ አለመሄዳቸውን እንዲሁም፤ ዜጎችም እንደልብ ወጥተው እየገቡ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህንን በዘላቂ መንገድ ለመፍታት የተጠናከረ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አንስተው፤ ከሽምግልና ባሻገር ፖለቲካዊ ውስኔ መወሰንም ተገቢ መሆኑን ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ