ሰኔ 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከ450 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ከሀገር ውጪ፤ 11 ሚሊዮን ገደማ ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ለሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት ዕድል እንደተፈጠረላቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ኤርሚያስ በድሉ ‎ወጥ የሆነ አሰራር አለመኖሩ ተግዳሮት መሆኑን ለአሐዱ የገለጹ ሲሆን፤ ከሁለት ዓመታት ወዲህ የተሻለ አሰራር መኖሩን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት አዲስ የተዘረጋው ‎አሰራር ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ ዜጎችን ከመነሻቸው ጀምሮ እስከ መዳረሻቸው ድረስ መከታተል የሚያስችል እና በሀገሪቱ ያሉትን 1 ሺሕ 400 ኤጀንሲዎችን እና በውጪ ሀገር ያሉ ከ4 ሺሕ በላይ ኤጀንሲዎችን መከታተል የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

"‎በበጀት ዓመቱ የሥራ ስምሪቱን በቴክኖሎጂ በማዘመን፣ የመዳረሻ ሀገራትን በማስፋት እና ከባለድርሻና ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት፤ የዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል" ሲሉም መሪ ሥራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል።

‎ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሆኖ ሳለ፤ በዘርፉ ላይ ዜጎች የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው እና ዜጎች እምነት እንዳይኖራቸው ሲደረግ የቆየ በመሆኑ በዘርፉ የሚስተዋል ችግር እንደነበር አንስተው፤ አሁን ላይ ግን ዜጎች የተሻለ አመለካከት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

በተያያዘ መረጃ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 41ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡

የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን በተመለከተ ቀደም ሲል ሲሠራባቸው የነበሩት አዋጆች ክፍተቶች የነበሩባቸው በመሆኑና በጊዜ ሂደት አዋጆቹ ያላካተቷቸውን ጉዳዮችን በመለየት ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አዋጅ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የቀድሞቹ አዋጆች የቤት ውስጥ ሠራተኛ፣ የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ ውጭ የትምህርት ዝግጅት የማይጠይቁ የሥራ ዓይነቶችን ባለማካተታቸው ክፍተቶች የተፈጠሩ ስለመሆኑ፤ በምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ (ዶ/ር) ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ አመላክተዋል፡፡

አዋጁ ሕገ- ወጥ የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪትን ለመከላከልና በውጪ ሀገር ሥራ ስምሪት የዘመነ የአንድ ማዕከል የአሠራር ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችልም ተጠቁሟል፡፡

በውጪ ሀገራት ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች መብታቸውና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚያስችል ላኪ ኤጀንሲዎች ተመጣጣኝ የዋስትና ገንዘብ እንዲያስቀምጡ፤ በማድረግ የዜጎች እንግልት የሚያስቀር አዋጅ ስለመሆኑም በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተብራርቷል።

Post image

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ ዜጎች በሰለጠኑበት ሙያ ብቃታቸውን በቴክኖሎጂ በማረጋገጥና ከዚህ ቀደም የነበሩ ተግዳሮቶችን በማስቀረት እንደ ሀገር ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችል ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ የሙያ መስኮች የካበተ ልምድ ኖሯቸው መደበኛ ትምህርት ያልተከታተሉ ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ የብቃት ምዘና ስርዓትንም መከተል እንደሚገባ በአዋጁ ስለመደንገጉም ሚንስትሯ አስገንዝበዋል፡፡

በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1389/2017 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ