መስከረም 27/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ወጋገን ባንክ አጠቃላይ ገቢው 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ እና ከታክስ በፊት 3 ነጥብ 85 ብር ትርፍ እንዳስመዘገበ በዛሬው ዕለት አስታውቋል።
ባንኩ ይህንን መጠን ያለው ትርፍ ሲያዝመዘግብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የገለጸው ባንኩ፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ73 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጿል
ወጋገን ባንክ አ.ማ. ይህን ያለው፤ ዛሬ መስከረም 27 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው።
በዚህም ጉባኤ ላይ ባንኩ በ2024/25 በጀት ዓመት በታሪኩ ከፍተኛ የሆነውን 13 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ማስመዝገቡን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሰብሳቢ አብዲሹ ሁሴን ገልጸዋል።

ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ38 በመቶ እድገት በማሳየቱ ምክንያት፤ የአንድ አክሲዮን ትርፍ 46 ነጥብ 10 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል።
ባንኩ ካስመዘገባቸው ዋና ዋና ስኬቶች መካከል፤ የተቀማጭ ገንዘብ እድገት አንዱ ነው ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው፤ ይህም 66 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል።
የተቀማጭ ገንዘቡ እድገት 28 በመቶ ሲሆን፤ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የተሰጠው ብድር መጠን 53 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ደርሷል ተብሏል።
የባንኩ ጠቅላላ ካፒታልም በ39 በመቶ በማደግ 12 ነጥቦ 8 ቢሊዮን ብር ሲደርስ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ29 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በባንክ አገልግሎት ተደራሽነት እና በሴቶች አካታችነት ዙሪያ ባካሄደው ምዘና ወጋገን ባንክ ከ30 የግል ንግድ ባንኮች መካከል ሁለተኛ ደረጃን መያዙን አቶ አብዲሹ አብራርተዋል።
የባንኩ ባለአክሲዮኖች ብዛት 14 ሺሕ 871 መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የወጋገን ባንክ አጠቃላይ የሠራተኞች ቁጥር 5 ሺሕ 553 መድረሱም ተነግሯል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ