መስከረም 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኳንተም ቴክኖሎጂ እና ከኦሮሚያ ባንክ ጋር በመሆን መንገደኞች ከተጓዙ በኃላ የበረራ ክፍያቸውን መፈፀም የሚችሉበትን የዲጂታል ብድር አሰራር በይፋ አስጀምሯል።
ሦስቱ ተቋማት 'ሚልኪ ዲጂታል' የብድር አገልግሎትን በመጠቀም በ'አሁን ይብረሩ፤ በኋላ ይክፈሉ' (Fly Now, Pay Later) መርኃ-ግብር አብሮ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በትናንትናው ዕለት ተፈራርመዋል፡፡

በዚህም ኦሮሚያ ባንክ በቅርቡ ሥራ ላይ ያዋለውን ሚልኪ ዲጂታል የብድር አገልግሎት መተግበሪያ በመጠቀም፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች ገንዘብ ቢያጥራቸው ያለምንም ማስያዣያ እና ዋስትና በሚልኪ ተበድረው የበረራ ቲኬት በመቁረጥ ከበረሩ እና ጉዳያቸውን ከፈፀሙ በኋላ ተረጋግተው የሚከፍሉበት አይነተኛ አማራጭ መመቻቸቱ ተነግሯል፡፡
በዚህም መሠረት ደንበኞች ጊዜያዊ የገንዘብ እጥረት ሳያሳስባቸው 'ሚልኪ መተግበሪያ'ን በመጠቀም፤ የአየር ቲኬታቸውን በመቁረጥ ሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ካከናወኑ እና ጉዳያቸዉን ከፈፀሙ በኋላ ስራቸዉን እየሰሩ እንዲከፍሉ እድል ተፈጥሮላቸዋል ተብሏል፡፡

የሦስቱ ተቋማት እስትራቴጂካዊ አጋርነት የጥሬ ገንዝብ ዝውውርን በመቀነስ፤ የኢትዮጵያን ዲጂታላይዜሽን ጉዞ ከማዘመን እና የፋይናንስ አካታችነትን ከመደገፍ በተጨማሪ የዜጎችን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በእጅጉ ያሳልጣል ተብሎ እንደሚታመን ተነግሯል።
ኦሮሚያ ባንክ ከኳንተም ቴክኖሎጂ ጋር በትብብር የበለጸገውን 'ሚልኪ ዲጂታል የብድር አገልግሎት መተግበሪያ'ን በመጠቀም ለተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘረፈ ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ የተገለጸም ሲሆን፤ በዚህም ባለፉት 4 ወራት 70 ሺሕ ለሚደርሱ ዜጎች 200 ሚሊየን የሚደርስ ብድር መሰጠቱን አስታውቋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ