ሰኔ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር እንዲሁም በሕክምና መሳሪያዎች ጥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘቱን ተከትሎ፤ በዛሬው ዕለት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ከኢትዮጵያ አክሪዴቴሽን አገልግሎት እውቅና ተቀብሏል።

ከዚህ ቀደም የመድኃኒት ጥራት ምርመራ ላቦራቶሪው በISO 17025 /2011 ዓ.ም የመጀመሪያውን እውቅና ማግኘት እንደቻለ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሄራን ገርባ ገልጸዋል።

Post image

ከዚህ በተጨማሪም በኮንዶም ጥራት ምርመራ በ2012 ዓ.ም በ5 መለኪያዎች በISO 17025፣ በ2022 የመድኃት ኢንስፔክሽን በአይሶ 17020፣ በ2023 ምግብ ጥራት ምርመራ ላቦራቶሪ እንዲሁም፤ በ2023 በሕክምና ጓንት ጥራት ምርመራ እውቅና ማግኘቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የተገኘውን እውቅናም ማስቀጠል ስለመቻሉ ተናግረዋል።

"በቅርቡ ደግሞ በሲሪንጅ ሁለት መለኪያዎች እና በፈጣን መመርመሪያ ኪት በ4 መለኪያዎች አዲስ ዓለም አቀፍ እውቅና ከዓለም አቀፍ አክሪዲቴሽን ቦርድ አይሶ 17025/2017 አግኝተናል" ብለዋል።

ይህ እውቅናም ጥራቱ የተጠበቀ ምግብና መድኃኒት ወደ ሕብረተሰቡ እንዲደርስ የማድረግ ሂደትን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ማግኘት መቻሉ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል እንደሆነ የገለጹት ደግሞ፤ የኢትዮጵያ አክሪዴቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦንሳ ባይሳ ናቸው።

በፕሮግራሙ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ እስካሁን በምግብና መድኃኒት ዘርፍ 43 እንዲሁም በሕክምና ግብአት ደግሞ 5 በአጠቃላይ በ48 ዘርፍ እውቅና መገኘቱን ገልጸዋል።

Post image


የጤና ሚኒስቴር ዲኤታ የሆኑት ዶ/ር ደረጄ ድጉማ እና ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው፤ ይህ እውቅና የኢትዮጵያን ምግብና መድኃኒት ቁጥጥርና ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ የሚያግዝ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲገኝ ላደረጉ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሥራ ክፍሎች፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ደምና ህብረህዋስ ባንክ አገልግሎትን ጨምሮ ለሌሎች ባለድርሻ ለሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች የእውቅናና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

Post image

የኢትየጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የሚካሄደውን የምግብና ጤና ግብዓቶች ቁጥጥር በማዘመን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ተቆጣጣሪ ተቋም ለመሆን በርካታ ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ተብሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ