ሰኔ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አዋሽ ባንክ እ ኤ አ ሰኔ 30 በተጠናቀቀው የ2024/25 የሒሳብ ዓመት 64 ቢሊዮን ገቢ ማስመዝገቡን የገለጸ ሲሆን፤ በዚህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ77 በመቶ እድገት ማሳየቱን አስታውቋል፡፡

የባንኩ ያልተጣራ ትርፍ ከግብር በፊት 22 ቢሊዮን በር ማግኘቱን የገለጹት የባንኩ ፕሬዝዳንት ጸሐይ ሽፈራው፤ "ይህም ካለፈው ዓመት 113 በመቶ እድገት አሳይቷል" ብለዋል።

ከዚህ በተጨመሪም የካፒታል መጠኑ ከነበረው 10 ቢሊዮን ወይንም 37 በመቶ እድገት ማሳየቱን አንስተው፤ ከ37 ቢሊዮን በላይ መድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

Post image

በተያዘው ዓመት ብቻ "አዋሽ ለሁሉም" በሚል የዲጂታል መተግበሪያ ያለምንም ማስያዣ፤ ከ301 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች ከ493 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ብድር መስጠቱን አስታውቀዋል።

ባንኩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 52 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት እና አጠቃላይ 989 ቅርንጫፎችን በመያዝ እና ዋና ዋና ሥራዎች ላይ አመርቂ ውጤት ያመጣበት ዓመት መሆኑንም አብራርተዋል።

በዚህ ዓመት በዲጂታል የተከናወኑ የገንዘብ ዝውውሮች በተመለከተ 1 ትሪሊዮን ብር መድረሱንም አንስተዋል።

በዚህም የትምህርት ስርዓቱን ዲጂታል ለማድረግ በሚደረገው ጥረት መሠረት፤ ከ2 ሺሕ 300 ትምህርት ቤቶች የአዋሽ ኢ ስኩል ማኔጅመንት ሲስተም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን እና 3 ነጥብ 2 የሚሆኑ ተማሪዎች በመተግበሪያው ክፍያ እንዲፈጽሙ መደረጉን አብራርተዋል።

Post image

በተጨማሪም በተለያየ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከመደገፍ አንጻር፤ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በማውጣት ማህበራዊ ግዴታውን መወጣቱን የባንኩ ፕሬዝዳንት ጸሐይ ሽፈራው ገልጸዋል።

በተለይ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ቡግና ወረዳ በድርቅ ለተጎዱ ከ10 ሚሊዮን ብር በማውጣት የዱቄትና የምግብ ዘይት እርዳታ ማድረጉን፣ በትግራይ ክልል ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት የጸጥታ ችግር ለወደሙ ትምህርት ቤቶች የሚውል ቁሳቁስ ማቅረቡን እንዲሁም፤ በገዜ ጎፋ በመሬት መንሸራተት ለተጎዱና መቄዶንያን ጨምሮ መሰል ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ ሲያደርግ መቅየቱን አንስተዋል።

በዚህ ዓመት 106 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ በአጠቃላይ የተቀማጭ ሒሳብ መጠን 332 ቢሊዮን ብር ማድረሱን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም መንግሥት ባስቀመጠው ፖሊሲ ማሻሻያ ባንኩ በወሰደው የውስጥ አሰራር መሠረት፤ ከ2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

ባንኩ በተያዘው ዓመት ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ደንበኞች ከ10 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ፋይናንስ ያደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ለአገልግሎት ተጠቃሚ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ፋይናንስ ማድረግ መቻሉን ተነስቷል።

የዲጂታል ብድር ከገልግሎት ይበልጥ እንዲሳለጥ ለማድረግ ከኢትዮ ቴሌኮምና ከሳፋሪኮም ጋር በጋራ ለመስራት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የመደበ ሲሆን በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡም አመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ