ሰኔ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ማብሰያዎችን ጨምሮ ከሌሎች ባህላዊ መጠቀሚያዎች የሚወጣው ጭስ ከደን መራቆት በተጨማሪ ነዋሪዎችን ለመተንፈሻ አካላት ችግር እያጋለጠ መሆኑ ተገልጿል።
ጭሱ በሚያስከትለው የአየር ብክለት ምክንያት የሚያጋጥመው የሞት መጠንም፤ በገዳይነታቸው ከተዘረዘሩ የሞት ምክንያቶች መካከል 4ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ከባህላዊ ማብሰያ መንገዶች ጋር ተያይዘው በሚከሰቱ የመተንፈሻ አካላት የጤና ችግሮች ምክንያት በየዓመቱ 63 ሺሕ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ የ150 ሺህ ሄክታር መሬት ደን እንደሚወድም አሐዱ ከተቋሙ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር የኢነርጂ ዘርፍ አማካሪ ጎሳዬ መንግስቴ፤ በታዳሽ ኃይሎች በቀላሉ ሊተኩ በሚችሉ ባህላዊ ማብሰያዎች ምክንያት የሚደርሰውን የጤና ችግር ለማቃለል የተደረገው ጥረት በሚፈለገው ልክ አለመሳካቱን አንስተዋል።
"ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ የዋሉት ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች ትኩረት ማገዶን መቆጠብ እንጂ በካይ ጭሶችን ማስወገድ አልነበረም" ያሉት አቶ ጎሳዬ፤ መሳሪያዎቹ በፋብሪካ አለመመረታቸው፣ ለሁሉም የምግብ ዓይነቶች በሚያገለግሉበት መንገድ ዲዛይን አለመደረጋቸው፣ እና ተያያዥ ጉዳዮች በሚፈለገው መልኩ ለውጥ እንዳይመጣ ካስገደዱ ምክንያቶች ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ዘርፉ አነስተኛ ትኩረት ሲሰጠው እንደቆየ አስታውሰው፤ "አሁን ችግሩን በእጅጉ መቀነስ የምዕተ-ዓመቱ የልማት ግብ አካል የሆነውን ንፁህ የማብሰያ ቴክኖሎጂ የማቅረብ ዕቅድ ለማስፈፀም "የማብሰያ ቴክኖሎጂ ልማት" የተሰኘ ፍኖተ ካርታ ይፋ ተደርጓል" ብለዋል።
በ2018 ወደ ትግበራ የሚገባው ፍኖተ ካርታው በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ 76 በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ሕዝብ የንፁህ የማብሰያ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎለታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ