ጥቅምት 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የፍራፍሬ መጠጦች ደረጃን ይፋ ባደረገበት ወቅት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የፍራፍሬ ጭማቂ ወይም ጁስ የሚያመርት አንድም ፋብሪካ እንደሌለ አስታውቋል፡፡

ባለሥልጣኑ በሀገር ውስጥ የሚመረቱት ከአልኮል ነጻ ለስላሳ መጠጦች የፍራፍሬ ቃና ወይም (Fruit Flavor) ብቻ መሆናቸውን ገልጿል።

Post image

በባለስልጣኑ የእንስሳት ተዋጽኦና አልሚ ምግብ ዴስክ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሑሴን ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ አንድ የፍራፍሬ ጫማቂ ጁስ ተብሎ እንዲጠራ ቢያንስ የመጠጡ 30 በመቶ የተፈጥሮ ፍራፍሬ ሊካተትበት ይገባል።

የፍራፍሬ ይዘቱ 30 በመቶ በታች ከሆነ የፍራፍሬ ጭማቂ ተብሎ እንደማይጠራ አብራርተዋል፡፡

አቶ መሐመድ ሑሴን በተጨማሪም፤ "በሱፐርማርኬቶች እና በመደብሮች ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የሀገር ውስጥ ምርቶች ጁስ የሚያስብላቸውን መስፈርት አላሟሉም" ብለዋል፡፡

ምርቶቻቸውን ጁስ ወይም የፍራፍሬ ጭማቂ በሚል መጠሪያ ያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች የጁስ ደረጃን ባለማሟላታቸው ሙሉ በሙሉ እንዲታገዱ ተደርጎ፤ “ፍሩት ፍሌቨር ድሪንክ” በማለት እንዲሠሩ መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል።

Post image

ባለሥልጣኑ ዜጎች በምርቶቹ አጠራር እንዳይደናገሩና የፍራፍሬ ጭማቂ በሚል ስያሜ ገበያ ላይ የቀረቡት ሁሉ የጁስ ደረጃን የማያሟሉ እና ከ30 በመቶ በላይ የፍራፍሬ ጭማቂ በውስጣቸው የሌለ እንደሆነ ግንዛቤ እንዲወሰድ አሳስቧል፡፡

የፍራፍሬ ቃና (ፍሩት ፍሌቨር) ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የፍራፍሬ መጠጦችም የጁስ መስፈርቱን አሟልተው እንዲገቡ አስፈላጊው ቁጥጥር እንደሚደረግ ተጠቁሟል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ