ጥቅምት 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት የግል ድርጅቶች ከሠራተኞቻቸው ደመወዝ ላይ ለጡረታና ለገቢ ግብር በሚል እየቆረጡ ቢሆንም፤ ተገቢውን ከፍያ ለመንግሥት ገቢ እንደማያደርጉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል።
በከተማዋ በሚገኙ አንዳንድ ተቋማት ከሠራተኞቻቸው ደመወዝ መንግሥት በማያውቀው መልኩ እንደሚቆረጥባቸውና ጉዳዩም አሳሳቢ እንደሆነ አሐዱ በደረሰው ጥቆማ መሠረት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮን ስለጉዳዩ ጠይቋል፡፡
በዚህም የግል ድርጅቶች ከሠራተኞች ደመወዝ የገቢ ግብርና የጡረታ ክፍያ በትክክል የሚከፍሉ የግል ድርጅቶች ከ40 በመቶ እንደማይበልጡ እና ቀሪዎቹ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ መንግሥት በማያውቀው መንገድ ገንዘቡን እንደሚቆርጡ የቢሮው የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሰውነት አየለ ለአሐዱ በሰጡት ምላሽ ገልጸዋል።
ኃላፊው በአዲስ አበባ ከተማ የደመወዝ ግብር በትክክል የማይከፍሉ የግል ተቋማት ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ገልጸው፤ ቢሮው ችግሩን ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይም በደረጃ 'ሀ' ግብር ከፋይ ሆነው በትክክል የማይከፍሉት ከ60 በመቶ በላይ ናቸው ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፤ መሰል ቅሬታ እና ጥቆማም ቢሮ እንደሚደርሰው ኃላፊው ገልጸዋል።
አክለውም በመሰል ሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ እየተሳተፉ ያሉ ድርጅቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማሳሰብ፤ ሙሉ ለሙሉ ችግሮችን ለመፍታትም ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ጥቆማ በመስጠት ትብብር ማድረግ እንሚገባው ገልጸዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት የግል ድርጅቶች ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ ለጡረታና ለገቢ ግብር በሚል እየቆረጡ ቢሆንም ተገቢውን ከፍያ ለመንግሥት ገቢ እንደማያደርጉ ተገለጸ