ጥቅምት 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት ማለትም ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ 151 ሺሕ 969 ነጥብ 41 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 622 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።
ይህ የተገኘው ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 243 ነጥብ 73 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ያለው መሆኑ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሣህለ ማርያም ገብረ መድኅን ለአሐዱ እንደተናገሩት፣ ይህ ከፍተኛ ገቢ የተገኘው አዳዲስ የገበያ መዳረሻ ሀገራትን በማስፋት በተደረገው ጥረት ነው።
የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚው፤ "በዚህ ሦስት ወር ውስጥ የተገኘው ገቢ ከፍተኛ ነው። ይህ ገቢ የተገኘው አዳዲስ የገበያ መዳረሻ ሀገራትን እንዲኖር በመደረጉ ነው።" ብለዋል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት ሦስት ወራት ውስጥ የተላከው ቡና ከፍተኛውን ገቢ ያስገኘው ጀርመን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ቤልጂየም በተላኩት እንደሆነ ባለሥልጣኑ ገልጿል።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት በዋናነት የማትታወቀው ቻይና በዚህ ዓመት በተሠራው የማስተዋወቅ ሥራ ምክንያት ከፍተኛ የቡና ምርት ከሚላክባቸው ሀገራት መካከል ከፍተኛውን ድርሻ እንደያዘች አቶ ሣህለ ማርያም ተናግረዋል።
በገቢ ቅደም ተከተል ከ1ኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ጀርመን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ቤልጂየም ሲይዙ፤ 4ኛ ቻይና፣ 5ኛ አሜሪካ፣ 6ኛ ደቡብ ኮሪያ፣ 7ኛ ዩናይትድ ዓረብ ኤሚሬትስ፣ 8ኛ ጃፓን፣ 9ኛ ጣሊያን እና 10ኛ ራሽያ መሆናቸው አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ የእነዚህ ዋናዎቹ አስር መዳረሻ ሀገራት አፈጻጸም ከ2017 ዓ.ም. አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር በመጠን 3 በመቶ እና በገቢ ደግሞ 52 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ባለሥልጣኑ ገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ