ጥቅምት 7/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ባለፉት አምስት ዓመታት በጤናው ዘርፍ የሚደረጉ የውጭ ድጋፎች እየቀነሱ መምጣታቸውንና ድጋፎች ሲቀንሱ እንደችግር ብቻ ሳይሆን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አዳዲስ አቅሞችን በማሳደግ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በመቋቋም እየተሰራ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።
በድጋፎች መቀነስ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመቋቋም መንግሥት ለጤናው ዘርፍ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ወደ ሥራ መግባቱን ለአሑዱ የተናገሩት፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚኒስትር ዴኤታ ደረጄ ዱጉማ (ዶ/ር) ናቸው።
በዚህም መሠረት ችግሮችን ለመቀነስ የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ግዢ በመፈፀም እንዲሁም በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥረቶች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በጤና መድን ስርዓት ከ63 ሚሊዮን ዜጎች በላይ ታቅፈው አገልግሎት እያገኙ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዚህም ተግባርም ለዘርፉ የሚውል ወደ 20 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
በዋናነትም አማራጭ የጤና ፋይናንስን በመጠቀም፤ ከግል እና ከሌሎች ተቋማት ሀብት የማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
"በአጠቃላይ የድጋፎች መቀነስ የተወሰኑ ክፍተቶችን ቢፈጥርም በታሰበው ደረጃ ሀገሪቱ ችግር ላይ አልወደቀችም" ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል። ከዚህ ባሻገርም በራሳችን ጤና ስርዓት ችግሮችን መቋቋም ተችሏል ብለዋል።
በድጋፎች መቀነስ ምክንያት ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ መንግሥት የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ግዢ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት ዓመታት ከበርካታ አጋር ድርጅቶች ጋር ሰፋፊ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሰል ድጋፎች በመቀነሱ የጤና ስርዓታቸው መናጋቱን የጠቁሙት ሚኒስትር ዲኤታው፤ በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ዋና ዋና አገልግሎቶች ላይ ግን ይሕ አላጋጠማትም ነው ያሉት።
ሚኒስቴር ዴኤታው አያይዘውም፤ "ለጤናችን የትኛውንም ሀገር ወይም አጋር ድርጅት ሳንጠብቅ በራሳችን የመስራት አቅማችንን ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል" ሲሉ አሳስበዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በጤናው ዘርፍ የውጭ ድጋፎች እየቀነሱ ቢመጡም አማራጭ የጤና ፋይናንስ ዘዴን በመጠቀም እየሰራ እንደሚገኝ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ
