ጥቅምት 7/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን በግንባታ ቦታዎች ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን በፍጥነት ለመመዝገብና ለመቆጣጠር የሚያስችል የሞባይል አደጋ ጥሪ መተግበሪያ ማበልጸጉን አስታውቋል።

አዲሱ መተግበሪያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሱ አደጋዎችን ቁጥርና መንስኤያቸውን በተመለከተ የተደራጀና የጸዳ መረጃ ለመያዝ ያለመ ነው ተብሏል።

የባለስልጣኑ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ግንባታ ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈፃሚ በረከት ተዘራ (ኢ/ር) ከአሐዱ ሬዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ መተግበሪያው በቀጣይ ሳምንት ይፋ ይደረጋል።

መተግበሪያው በግንባታ ቦታዎች ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን፣ የጉዳቱን መጠንና መንስኤውን በትክክል መመዝገብ የሚችል ሲሆን፤ ይህም በዘርፉ ያሉ የአደጋዎችን ምንነት በማረጋገጥ፣ መረጃን በዳታ ቤዝ ለማደራጀት ያስችላል ብለዋል።

መተግበሪያው ከብሔራዊ መረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመቀናጀት የበለጸገ ሲሆን፤ ይህ ትብብርም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማሻሻል የሚያስችል የጋራ ሥራ መስራትን የበለጠ እንደሚያቀለው ኢንጂነር በረከት ገልጸዋል።

መሪ ሥራ አስፈፃሚው ለመተግበሪያው የተሰጠው የሙከራ ጊዜ ሁለት ዓመት እንደሆነ ገልጸው፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ መተግበሪያውን ተደራሽ የማድረግ ሥራ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

አክለውም፤ የትኛውም አስገንቢ አካል የሚገነባውን ሕንፃ አስቀድሞ ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን በማሳወቅ፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ አደጋዎችንና የሚነሱ የጥራት ችግሮችን አስቀድሞ ማስቀረት እንደሚቻል ተናግረዋል። አስገንቢ አካላትም በባለቤትነት ስሜት ወደ ተቋሙ በመምጣት እንዲያመለክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

‎#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ