ጥቅምት 7/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በፍርድ ቤት ከሚሰጥ ትዕዛዝ ወይም በሕግ በግልፅ ከተደነገገው ውጭ ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ መቁረጥ የአስተዳደር በደል በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ለተለያዩ ሥራዎች በሚል ያለ ፈቃዳቸው ደመወዛቸውን ይቆረጣል የሚል ቅሬታ ለተቋሙ እንደሚያቀርቡ ተጠቁሟል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ በርካታ መምህራን፣ የጤና ባስሙያዎች እና ሌሎች ሠራተኞች ፈቃዳቸውን ሳይሰጡ ከደመወዛቸው ላይ እየተቆረጠባቸው መሆኑን እንደተናገሩትም ተገልጿል።

ቅሬታ አቅራቢዎች መፍትሄ እንዲሰጣቸው በተለያዩ ጊዜያት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም አዋሳ ቅርንጫፍ ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አንለይ ወርቄ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዳውሮ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ መምህራን ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረባቸውን አንስተዋል።
ይህም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሠራተኞች ስምምነታቸውን በጽሑፍ ሳይገልጹ ከደመወዛቸው ላይ መቆረጡ በገልፅ ከተደነገገው መርህ ጋር የሚቃረን እንደሆነ አመላክተዋል።
በመሆኑም ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ተገቢ እርምት ሊደረግ እንደሚገባ ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ