ሕዳር 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአሁኑ ወቅት በደቡበ ኢትዮጵያ ክልል በጅንካ ከተማ ምንነቱ በመረጋገጥ ላይ ያለ የሄሞራጂክ ፊቨር (Hemorrhagic fever) በሽታ መከሰቱን የቅኝት መረጃዎች አመላተዋል ሲል ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
እስከአሁን ድረስም ስምንት ሰዎች (08) በበሽታው የተጠረጠሩ መሆኑ ስለመታወቁን ነው ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በመሆን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የገለጸው፡፡

በዚህም መሰረት የጤና ሚኒሰቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተመዘገበውን ይህንን የበሽታ መንስኤ ለማወቅ እና ተጨማሪ ስርጭትን ለመግታት እንዲሁም ለመቆጣጠር ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ወደቦታው መላኩን ገልጿል፡፡
በዚህ የመስክ ግምገማዎች እና የላብራቶሪ ምርመራዎች እየተከናወኑ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በተጨማሪም የማህበረሰብ ቅኝት፣ የንክኪ ልየታ፣የቤት ለቤት ልየታ እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን እያጠናከረ ይገኛል ተብሏል።
በመሆኑም መላው ሕብረተሰብ እና የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሌላ ተጨማሪ መግለጫ እስከሚሰጥ ድረስ፤ ለመከላከል የሚከተሉትን ምክረ-ሃሳቦች እና ጥንቃቄዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡
👉 በአፍ፣ አፍንጫ እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የመድማት፣ ትኩሳት፣ ማስቀመጥ እና ማስመለስ ምልክት ሲኖር፤ ወደ ሕክምና ተቋማት መሄድና በወቅቱ የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረግ፣
👉 ምልክት ከታየበት ማንኛውም ሰው ጋር ንክኪ በሚኖርበት ጊዜ ራስን የመከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም፣
👉 ሁልጊዜ እጅን በሳኒታይዘር ወይም በውሃና በሳሙና በመታጠብ ማጽዳት፣
👉 ማንኛውም ጤና ተቋም በታካሚዎች ልየታ አካባቢ ልዩ ትኩረት በመስጠት የቫይራል ሄሞሬጅክ ፊቨር (Viral Hemmoragic fever) መሰል በሸታ መለየት፣ መመርመር፣ ማከም እና ሪፖርት ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጨማሪ መረጃዎችን ወደ 8335 እና 952 ነጻ የስልክ መስመሮች በመደወል ማግኘት እንደሚቻል አስታውቋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ