የኢፌዴሪ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የሩብ ዓመት ሪፖርት ካደመጠ በኋላ በርካታ ጥያቄዎችንና ምክረ ሐሳቦችን አቅርቧል።

Post image

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስቴር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውን የሩብ ዓመት ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።

ሚኒስቴሯ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኢትዮጵያን ባህል ለማስተዋወቅ በትኩረት እየሠራ መሆኑን፣ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ፍሰት እየጨመረ መምጣቱን እንዲሁም፤ የኢትዮጵያን ባህል ወደ ውጭ በመውሰድ የማስተዋወቅ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል።

በተያያዘም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩ በዓላትን በአንድነት በማክበራቸው የሕዝቦች አንድነት እየተጠናከረ መምጣቱን አብራርተዋል። ከሥነጥበብና ፈጠራ ጋር በተያያዘም ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ጭምር ውይይት የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በሩብ ዓመቱ ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ አውደ ርዕይ ተዘጋጅቶ በፌዴራል ደረጃ ውድድር የተካሄደበት መሆኑንም አብራርተዋል።

Post image

በብሔራዊ ቲያትር ደረጃ ወደ 55 ሺሕ እንዲሁም በክልል ደረጃ ወደ 4 ሚሊዮን የኅብረተሰብ ክፍል የታደመበት ሂደት መከናወኑን አስታውቀዋል። በዚህም ምክንያት የኪነጥበብ ምክር ቤት የማቋቋም ሂደት መጀመሩን የገለጹት ወይዘሮ ሸዊት፤ ጥበብን በተደራጀ መንገድ ለመምራት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ገጽታ ለማስተዋወቅ በሰርከስ ትርኢቶች አማካኝነት በዚህ ሩብ ዓመት በአሜሪካ 44 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በእስያ አገራት 61 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ሚኒስቴሯ ገልጸዋል።

ከስፖርት ልማት ጋር በተያያዘ በአብዛኛው ስኬት የነበረበት ሩብ ዓመት መሆኑን የገለጹት ሚኒስቴሯ፤ በተለይም ከታዳጊዎች ጋር በሚሠሩ ሥራዎች የተሻለ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

የስፖርት ትምህርትና ሥልጠናን በሚመለከትም የስፖርት ውጤታማነት ሲጎድል ጥያቄዎች እንደሚበረቱ ገልጸዋል። ሆኖም "ሕዝብም ሆነ ምክር ቤቱ ውጤት የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት በመሆኑ በአንድ ጊዜ ውጤት ሊመጣ አይችልም" ብለዋል።

Post image

ወይዘሮ ሸዊት የረጅም ጊዜ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ሲገልጹ፤ በዚህ ዓመት እየተሠራ ያለው ሥራ ከአምስት ዓመትና ከስድስት ዓመት ጊዜ በኋላ ውጤቱ የሚታይ ሥራ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

"በዓለም መድረክ ተሳትፎ ብቻውን እንደ ስኬት ሊቆጠር ይገባል" ያሉት ወይዘሮ ሸዊት፤ "አሁን እየተወቀስን ያለነው በኛ ሥራ አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል።

በጃፓን ቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጣው ውጤት "ከኛ ወድሞ የተሠራ እንጂ እኛን የሚያስጠይቅ አይደለም" ሲሉ አስረድተዋል።

የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከአስተያየቶች በተጨማሪ፤ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት በመነሳት ጥያቄዎችን ሰንዝሯል።

Post image

የቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ዳውቦ ምሕረት፤ ከጥያቄዎቹ መካከል ብሔራዊ ቲያትርን በተመለከተ በ2017 ዓ.ም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባቀረበው ሪፖርት ላይ ያለአግባብ ከተፈጸሙ ክፍያዎችና ከደንብና መመሪያ ውጪ የተደረጉ ግዢዎች ጋር በተያያዘ የተነሳውን ክፍተት በሪፖርት ያላቀረበበትን ምክንያት ጠይቀዋል።

ሌላው በቋሚ ኮሚቴው አባላት ጥያቄ ያስነሳው ጉዳይ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያስመዘገበችው ውጤት ከ33 ዓመት በኋላ ዝቅተኛ ሆኖ ሳለ በስኬት መልክ መቅረቡ ነው።

በተለይም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቀረበው አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የተመለከተው መቶ በመቶ ስኬት ለጥያቄው መነሻ ሆኗል።

በብዙዎች የስፖርት ቤተሰቡ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞና ትችት ሲሰጥበት የቆየው የአትሌቲክስ ቡድን ውጤት ማጣት ተጠያቂ ከሆኑት ተቋማት አንዱ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተጠቃሽ ነበር። በተለይም በጃፓኑ የዓለም ሻምፒዮና የተገኘው ውጤት እንደ ሀገር አትሌቲክሱ ያለበትን ደረጃ ያመላከተ ሆኗል።

Post image

ይህንን በሚመለከት ከፍተኛ የሆነ ጥያቄ ሲነሳበት ለነበረው ለዚህ ውጤት ማጣት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ "እኔ ተጠያቂ ልሆን አልችልም" የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

ሚኒስቴሯ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በሰጡት ምላሽ፤ መሥሪያ ቤታቸው መጠየቅ ያለበት ከአምስትና ስድስት ዓመት በኋላ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ መፍትሔ ተተኪ ስፖርተኞች በአትሌቲክሱም ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሀገሪቱ በሚገኙ 31 ፌዴሬሽኖች ላይ እንደሚሠራ አብራርተዋል።

ከቋሚ ኮሚቴው በተነሳው የብሔራዊ ቲያትርን በተመለከተ በ2017 ዓ.ም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባቀረበው ሪፖርት ላይ ያለአግባብ ከተፈጸሙ ክፍያዎችና ከደንብና መመሪያ ውጪ ከተደረጉ ግዢዎች ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

በምላሻቸውም ከግንባታ ጋር በተያያዘ ለተፈጠረው ክፍተት ለዋና ኦዲተር ተልኮ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ስድስት ወር በግኝቱ ላይ የተነሳውን በሪፖርት እንደሚያካትቱ ሚኒስቴሯ ተናግረዋል።

ቋሚ ኮሚቴው የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ ሀገር ውስጥ መጥተው እንዲጎበኙ ከማድረግ በተጨማሪ፤ የኢትዮጵያን ባህል ወደ ውጭ ሀገራት ወስዶ በማስተዋወቅ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስቧል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተለያዩ አገሮች ጋር አብሮ ለመሥራት የተፈራረማቸውን ውሎች ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚገባም ጨምረው አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም የዕደ ጥበብ ሥራዎችን በመላ ሀገሪቱ ለማስፋፋት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትኩረት መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሁሉም ፌዴሬሽኖች በዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ከማስተናገድ ጋር በተያያዘ ሀገር አቀፍ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ ሲሆን፤ ከታዳጊ ጀምሮ በስፋት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑም ተገልጿል።

ስታዲየሞች የማጠናቀቅ እና አዳዲሶች የመሥራት ሥራው ተጠናክሮ እየተሠራ መሆኑንም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አብራርቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ