መስከረም 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት በ2018 በጀት ዓመት ከለጋሾች የሚሰበስበውን ደም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት በ30 በመቶ ብልጫ እንዲኖረው ማቀዱን አስታውቋል።
ይህ አዲስ እቅድ ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች 550 ሺሕ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ያለመ ነው።
የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ፤ በመስከረም ወር በሚኖሩ በዓላት ምክንያት በሚደርሱ አደጋዎች የደም እጥረት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት በመኖሩ አስቀድሞ አስፈላጊ ዝግጅት እየተደረገ ነው” ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
አቶ ሀብታሙ፤ የዚህ ዓመት እቅድ ባለፈው በጀት ዓመት ከተሰበሰበው 423 ሺሕ ዩኒት ደም ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው እቅድ 30 በመቶ ጭማሪ አለው ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በክረምት ወራት በተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንቅስቃሴ 90 ሺሕ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 86 ሺሕ 500 ዩኒት ደም መሰብሰቡን አስታውሰዋል።
ከተሰበሰበው 86 ሺሕ 500 ዩኒት ደም በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የተሰበሰበው 25 ሺሕ ዩኒት መሆኑ ተገልጿል።
የክረምቱ ደም የማሰባሰብ መርሃ-ግብር እስከ መስከረም 30 እንደሚቀጥል የተነገረም ሲሆን፤ እስካሁን ባለው ሂደት በርካታ በጎ ፈቃደኛ ተቋማት፣ ማህበራትና ግለሰቦች የተሳተፉበት ሰፊ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በዚህ ዓመት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች 550 ሺሕ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለጸ
