መስከረም 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ጊፍት ሪል እስቴት የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ለመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የቁሳቁስ እና ምግብ ነክ ጥሬ እቃዎችን በዛሬው እለት በድጋፍ መልኩ አበርክቷል።

ከዚህ በፊት በተለያየ ጊዜ ለመቄዶንያ ድጋፍ ማድረጉን የገለጸው ጊፍት ሪልስቴት ዛሬም በአጠቃላይ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ የፈጀ የቁሳቁስ እና ምግብ ነክ ጥሬ እቃዎችን ማለትም ፎም ፍራሽ ፣ የምግብ ዘይት እና ለእርድ የሚሆኑ ሁለት በሬዎችን በድጋፍ አበርክቷል።

Post image

በድጋፍ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የጊፍት ቢዝነስ ግሩኘ ባለቤትና ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብየሱስ ኢጋታ፣ የመቄዶንያ መስራች ክቡር ዶክተር ቢኒያም በለጠ፣ የመቄዶንያ ተወካይ አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው የመቄዶንያ አረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን ማህበር ተወካዩች፤ ለተደረገላቸው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ ዕለቱንም በጊፍት ሪል እስቴት ሥም በመሰየም በየዓመቱ እንደሚያከብሩት ገልጸዋል።

Post image

ጊፍት ሪል እስቴት የደንበኞችን ፍላጎት ከጊዜው ጋር ተመራጭ የሆነ ዲዛይንና አዳዲስ እሴቶችን በማካተት ከዚህ ቀደም ዘመናዊ መንደሮችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፉን ገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በለገሃር፣ በተክለ ሀይማኖት፣ በ22 ማዞሪያ ፣ በሲ ኤም ሲ እና በፈረስ ቤት ዘመናዊ እና ቅንጡ የመኖሪያ እና የንግድ አፓርትማ መንደሮችን እየገነባ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

በመንደሮቹም ትምህርት ቤቶች፣ የሕክምና ተቋማት፣ ሞሎች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች ከበቂ የመኪና ማቆሚያ ጋር ተካተዋል ተብሏል፡፡

ጊፍት ሪል እስቴት በጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ ውስጥ በ2005 ዓ.ም የተቋቋመ እና ምቹ እና የቅንጦት አኗኗር ዘይቤን የሚያራምዱ ዘመናዊ መገልገያዎችን ያሟሉ ምቹ ቤቶችን የመስራት ተልዕኮ አንግቦ የተቋቋመ ኩባንያ ነው።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ