መስከረም 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን እና ቱሪስቶችን ታላቁን የደብረ ከርቤ ንግሥ በዓል ለማክበር እና ለመታደም እንደሚመጡ በመገመት ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

ክልሉ ከዓመታዊው ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ክብረ-በዓል ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱም ተገልጿል።

የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ እምቢአለ፤ "ዝግጅቱ ከሐምሌ ወር ጀምሮ ሲደረግ የቆየ የተቀናጀ ሥራ ውጤት ነው" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

Post image


"ግሸን ደብረ ከርቤ" በዓመት ሁለት ጊዜ (መስከረም 21 እና ጥር 21 ቀናት) የሚከበር ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ሲሆን፤ የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የመስቀል ፍልሰትን ታሪክ የሚያስታውስ ነው። በተለይም የፊታችን መስከረም 21 ቀን የሚከበረው ዓመታዊ በዓል ከተለያዩ አካባቢዎች በሚሰባሰቡ ምዕመናን በድምቀት ይከበራል፡፡

በዓሉ ላይ የሚሳተፉ እንግዶችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል በቂ የጸጥታ ሥራ መሠራቱን የተናገሩት አቶ አበበ፤ በአንድነትና በፍቅር በዓሉን ለማክበርም ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ጋር በጋራ የዝግጅት ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።

ግሸን ማርያም በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በአምባሰል ወረዳ የምትገኝ ሲሆን፤ ላለፉት 563 ዓመታት የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓል ሲከበር መቆየቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች ዘንድ ይነገራል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ