ሰኔ 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል ባለው የመሠረተ ልማት ችግር ምክንያት፤ ለአራት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት እስካሁን መጀመር አለመቻሉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡

በክልሉ ጤና ቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዳይሬክተር አቶ በላይ አሊ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ ምእራብ ትግራይን ጨምሮ 93 ወረዳዎችን ማካከተት ቢቻልም እስካሁን ግን ሥራ አልተጀመረም፡፡

አሁን ላይ ለማህበረሰቡ አገልግሎቱን ለመስጠት በክልሉ 40 ሚሊየን ብር ተበጅቶ እየተሰራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

አክለውም፤ "በዋነኛነት የጤና መድህን አገልግሎት ላለመጀመሩ ዋና መንስኤ ተብሎ ከተነሱት መካከል ከጦርነት በኋላ ጤና ተቋማት መውደማቸው ነው" ብለዋል፡፡

ሌላው እንደምክንያት የሚነሳው ችግር ደግሞ፤ በጤና ተቋማት ላይ አስፈላጊ የሚባሉ መድኃኒቶች እና የበጀት እጥረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ማህበረሰቡ 'የአገልግሎት መቼ ነው የማገኘው ብር አውጥቼ' የሚል ስጋት ስላለ አሁን ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰራ ነው፤ ይህም ዳግም አገልግሎት ለመጀመር እና ማህበረሰቡ ላይ እምነት ለመፍጠር ያግዘናል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

"ከጦርነቱ በፊት የነበረውን ለጤና ተቋማት ያልተከፈለ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የአገልግሎት ክፍያ መክፈል ተችሏል" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን ከጤና መድህን ውጭ የሆኑ የነጻ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ክፍያን ለጤና ተቋማት መከፈል አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ የነበሩት ክፍተቶች እየተቀረፉ በመምጣታቸው ምክንያት፤ እስከዚህ ዓመት መጨረሻ ድረስ አገልግሎቱን ለመጀመር ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ