ሰኔ 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎የባሌ ሀገረ ስብከት በሚሊኒየም አዳራሽ ሊደርገው የነበርው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ከሰኔ 29 ቀን ወደ ጷግሜ 2 ቀን 2017 ማራዘሙን በዛሬው ዕለት አስታውቋል።

‎የገቢ ማሰባሰቢያው መርሐ ግብር የተራዘመው የሚሊኒየም አዳራሽ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት መሆኑም ተገልጿል።

‎ገቢው የሚሰበሰበው በችግር ላይ ለሚገኘው ለጎለ ብሕንሳ መካነ ሕይወት አቡነ ተክለሃይማኖት አንድነት ገዳም መነኮሳት እና መነኮሳይያት የሚውል መሆኑን የገዳሙ አበምኔት አባ ወልደ ሚካኤል ገብረ እግዚአብሔር ተናግረዋል።

‎ገቢው ለገዳሙ አረጋዊያን መነኮሳት ማረፊያ ቤት ለመስራት፤ መነኮሳቱ በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ የሽመና ማሽን መግዣያ እንዲሁም በበአታቸው ለማፅናት የታለመ መሆኑን የገዳሙ አበምኔት ገልጸዋል።

Post image

በዚህም የገዳሙን ችግር ለመፍታት ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር ኮሚቴ ተዋቅሮ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ የገቢ ማሰባሰቢያ ለማከናወን በዝግጅት ላይ ባለበት ወቅት፤ በሚሊኒየም አዳራሽ ላይ ጉዳት በመድረሱ በዛሬው ዕለት የጉባኤ ቀን ለውጥ መደረጉን ሀገረ ስብከቱ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

ከአዲስ አበባ 445 ኪ.ሜ ከጎባ ከተማ 30 ደቂቃ የእግር መንገድ ወጣ ብሎ በስተምዕራብ የሚገኘው ጎለ ብሕንሣ መካነ ሕይወት አቡነ ተክለሃይማኖት አንድነት ገዳም ከ250 በላይ ማህበረ መነኮሳት እና መነኮሳይያት በውስጡ እንደሚገኙ ተገልጿል። ‎

ገዳሙ የራሱ የሆነ የእርሻ መሬት የሌለው በመሆኑ የገዳማውያኑን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ በእጅጉ አስፈላጊ ነው ተብሏል።

‎ገዳሙ በባሌ ሀገረ ስብከት የሚገኙ ሲሆን የተመሰረተው በ1978 ዓ.ም በባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሰላማ ነው፡፡ ይህን ታሪካዊ እና ጥንታዊ ገዳም መደገፍ የሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ሀላፊነት በመሆኑ ጷግሜን 2 ቀን 2017 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ በመገኘት ለገዳሙ ድጋፍ እንዲያደረጉ ጥሪ ቀርቧዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ