ሰኔ 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን የቦሬቻ ወረዳ ነዋሪዎች በ2002 ዓ.ም ለአገልግሎት የሚያስፈልጉት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ቢዘረጉም እስካሁን አገልግሎት ማግኘት አልቻልንም ሲሉ ቅሬታቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

የተዘረጋው መሰረተ ልማት አገልገሎት ሳይሰጥ ከጥቅም ውጭ እየሆነ ነው በሚል ከማህበረሰቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ ይህን ተከትሎ 2013 ዓ.ም ላይ ዳግም የእድሳት ሥራ ቢጀመርም መቋረጡን እና እስካሁንም አገልግሎት መስጠት አለመጀመሩን አስረድተዋል፡፡

Post image

በወቅቱ የወዳደቀው የኤሌክትሪክ ምሰሶን ለመጠገን ሙከራ ተደርጎ እንደነበር በ፤ ነገር ግን ትራንስፎርመር ለማንሳት ሲሞከር 'ሌላ ምትክ ሳይመጣ አይነሳም' በሚል ማህበረሰቡ ክልከላ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

"ሆኖም እስካሁን የትራንፎርመር ቅያሪ አልተደረገም፤ እኛም ጨለማ ውስጥ ነን" ሲሉም ያለውን ችግር ገልጸዋል፡፡

አሐዱም የወረዳውን ነዋሪዎችን ቅሬታ በመያዝ የኢትዮጲያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ጠይቋል ፡፡

"መሰረተ ልማቱ ከተዘረጋ በኋላ የነበረው ፍላጎት አነስተኛ ነበር" ያሉት የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዋር አብራር፤ "ቆይቶ ግን የማህበረሰቡ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ዳግም ወደ ሥራ ሊገባ ሲል ከዚህ ቀደም ተዘርግቶ የነበረው መስመር አገልግሎት ባለመስጠቱ ብዙ ነገር መስተካክል ነበረበት" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Post image

አክለውም በ2013 ዳግም የእድሳት ሥራ ቢጀመርም ከዚህ ቀደም ተተክሎ የቆየው ለብልሽት በመዳረጉ ለአጭር ጊዜ የሚሆን 15 ኪሎ ቮልት ለመትከል መሞከሩን የገለጹ ሲሆን፤ "ነገር ግን አንዳንድ አካላት 'ቀድሞ የነበረው አይነት 33 ኪሎ ቮልት ይገጠምልን' የሚል ቅሬታ በማቅረባቸው ተቋርጦ ቆይቷል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

"ነገር ግን አሁን ላይ ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሰራ ነው" ያሉት የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ፤ ለዚህም በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ጥናት ተደርጎ በመጠናቀቁ በመጪው 2018 በጀት በመያዝ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ