መስከረም 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል በ58 ወረዳዎች አጎበር ለማቅረብ እና የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
በክልሉ ከሚገኙ 85 ወረዳዎች ውስጥ 58 በሚሆኑት ወረዳዎች የአጎበር ስርጭት እና የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ እቅድ መያዙን የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማሙሽ ሁሴን ለአሐዱ ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው ሁኔታም የጤና ሚኒስቴር በሁለት ዙር ከሚያቀርበው አቅርቦት የመጀመሪያው ዙር እየገባ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
"በተለይም ከመስከረም ወር በኋላ በሚከሰተው የወባ ስርጭት አስመልክቶ ቅድመ ዝግጅት ከማድረግ አንፃር ሰፋ ያለ ስራ እየተሰራ ነው" ብለዋል። ከእነዚህም መካከል አንደኛው ለወባ መራባት ምቹ በሆኑ አካባቢዎች ለታችኛው መዋቅር ማስገንዘብ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም መሠረት የወባ ንቅናቄ በሚል በተዘጋጀው መርሃግብር አማካኝነት፤ መሠረታዊ ምክንያቶችን በመለየት መስራት እንደሚገባ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የማሳወቅ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የጤና ተቋማት ዝግጅት ላይ ትኩረት መደረጉንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በዚህ አግባብ የጤና ተቋማት ለወባ ምርመራ የሚሆን የህክምና ግብዓት ስለመኖሩ እና የባለሙያዎችን አቅም የማሳደግ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
በሌላ በኩልም በክልሉ ትምህርት የተጀመረ በመሆኑ በተማሪዎች ስለ ወባ በሽታ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማስተማር፤ የተማሩትን ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው በማስተማር የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ አሁን ባለው ሁኔታው ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው የክልሉ ማህበረሰብ አጎበር ተደራሽ መሆኑን ጠቁመዋል።
ነገር ግን ከፍተኛ ጫና ይኖራል ተብሎ በተገመቱ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከሚቀጥለው ሳምንት በኋላ የኬሚካል ርጭት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ከ2 ዓመት በታች እና ከ6 ወራት በላይ ላሉ ሕጻናት የሚሰጠው የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ባለፈው ሳምንት በቁሊቶ ከተማ መጀመሩን አስታውቀዋል።
ይህም የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የክትባት አይነት ወደ 14 ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ