መስከረም 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕግ ታራሚዎች በቀጥታ ተንቀሳቃሽ ምስል ችሎት የሚከታተሉበትን ስርዓት ዳግም ለማስጀመር የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑን የሐረሪ ክልል ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

አሰራሩ ከአሁን ቀደም ይሰራበት እንደነበር የገለጹት የክልሉ ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኘነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማህዲ ማህመድ፤ አሁንም አሰራሩን ዳግም ለማስጀመር የግብዓት ርክክብ መደረጉን ለአሐዱ ተናግረዋል።

ስርዓቱ ከሀረሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ መቆየቱን ጠቁመው ዳግም ለማስጀመር የሚያስችሉ የቁሳቁስ ግብዓቶች ርክክብ መደረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም በማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ በተሻለ መንገድ በአዲስ ቴክኖሎጂ ለማስጀመር ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቁመው፤ አሰራሩ የሕግ ታራሚዎች ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ሳይጠበቅባቸው የችሎት መርሃ ግብር እንዲከታተሉ ያስችላል ብለዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ታራሚዎች የችሎት ጉዳያቸውን ለመከታተል በፀጥታ ሃይሎች ታጅበው እንደሚቀርቡ የገለጹት የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኘነት ዳይሬክተር፤ በተጨማሪም ጉዳያቸውን በቅርበት የሚከታተሉ የማረሚያ ተቋሙ ጉዳይ አስፈፃሚዎች እንዳሉ አንስተዋል።

በዚህም ምክንያት የሚፈጠር ማንኛውንም መጉላላት በማስወገድ በቀላሉ በተዘጋጀላቸው የተንቀሳቃሽ ምስል ኮንፈረንስ ክፍል በመግባት መከታተል ያስችላቸዋል ብለዋል።

ይህ አይነቱ አሰራር በተለይም በአንዳንድ የጥቅም ተጋሪ ሰዎች ምክንያት የሚደርስ ኪሳራን ማስቀረት እንደሚያስችል አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ከሰብዓዊ መብት አንፃር ኮሚሽኑ የሚሰጠውን አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

ታራሚዎች ወደ ፍርድ ቤት ከተወሰዱ በኋላ ያጋጥሙ የነበሩ የመጥፋት እንቅስቃሴዎችን በማስቀረት ረገድ አሰራሩ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የሐረሪ ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የሕግ ታራሚዎች እና ቤተሰቦችን መረጃ አያያዝ ከወረቀት አሰራር ወደ ዲጂታል በመቀየር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ዳይሬክተሩ አያይዘው አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ