መስከረም 19/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ በ80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የግብጽ ተወካይ ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር ኢትዮጵያን አስመልክቶ ላቀረቡት የሐሰት ክስ ምላሽ ሰጥታለች።

በመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ በኒውዮርክ በተካሄደው 80ኛው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 'እኔ ብቻ ልጠቀም' የሚል የቅኝ ግዛት ትርክትን ታሪክ በማድረግ በተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሀብት ትብብር አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት መርህ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም ተናግረዋል።

አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ በጠቅላላ ጉባኤው የሥነ ስርዓት ደንብ ላይ የተቀመጠውን ምላሽ የመስጠት መብት(First Right of Reply) ተጠቅመው፤ ግብጽ ላነሳችው ሀሳብ መልስ ሰጥተዋል።

የግብጽ ተወካይ በድጋሚ በኢትዮጵያ ላይ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎም፤ ኢትዮጵያ የሁለተኛ ምላሽ መብቷን ተጠቅማ (Second right of reply) በአምባሳደር ዮሴፍ አማካኝነት በድጋሚ መልስ ሰጥታለች።

አምባሳደር ዮሴፍ ኢትዮጵያ ግብጽ በቅርቡ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ላቀረበችው መሠረተ ቢስ ክስ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ተገቢውን ምላሽ መስጠቷን አውስተዋል።

Post image

ምላሹ እውነታ ላይ የተመሠረተና የግብጽ ተደጋጋሚ ትርክቶች ሐሰተኛ መሆናቸውን በግልጽ ያሳየ መሆኑን አመልክተዋል።

የናይል ወንዝ የተፋሰሱን ሀገራት ለዘመናት ያቆራኘ የተፈጥሮ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ይህን ትስስር ለማጥበቅ ስትሰራ መቆየቷን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ አጠቃቀም ላይ ለረጅም ጊዜ ትብብር ያማከለ አካሄድን ስትከተል መቆየቷን የጠቆሙም ሲሆን፤ በተቃራኒው ግብፅ 'ታሪካዊ መብት አለኝ፣ እኔ ብቻ ልጠቀም' የሚል ጊዜው ያለፈበት የቅኝ ግዛት እሳቤ እያራመደች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንዲተገበር በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸው፤ በአንጻሩ ግብጽ የሁለትዮሽ የቅኝ ግዛት ስምምነትን ለማስቀጠል በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ተገቢነት የሌለው ጫና እያሳደረች መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከግብጽ እና ከሱዳን ጋር በተፈራረመችው የመርሆዎች ስምምነት አማካኝነት የግድቡን ሙሌት እና ሥራ አስመልክቶ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ግልጽነት በተሞላበት ሁኔታ መረጃ ተደራሽ ስታደርግ መቆየቷን አብራርተዋል።

በሦስትዮሽ ድርድሩም ኢትዮጵያ ሁሉን አሸናፊ የሚያደርግ መንገድን ብትከተልም፤ ግብጽ ድርድሩን የሚያደናቅፉ ድርጊቶችን ስትፈጽም መቆየቷን ተናግረዋል።

ግብጽ በድርድሩ ወቅት 'የውሃ ባለቤትነትና ድርሻ ላይ ስምምነት መደረስ አለበት' በሚል ስታራምድ የነበረው ግትር አቋም ስምምነት እንዳይደረስ መሰናክል መፍጠሩንም አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ የግብጽን የቅኝ ግዛት ትርክትና 'እኔ ብቻ ልጠቀም' የሚል አባዜ ፈጽሞ አትቀበለውም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት ባደረገና ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የውሃ ሀብቷን እየተጠቀመች መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያ መሻት የዜጎቿን ሕይወት መቀየር፣ መልማትና ማደግ እንዲሁም ዜጎች፣ ሆስፒታሎች እና ፋብሪካዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ማድረግ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከርና ሽብርተኝነትን በመከላከል የጋራ ሥራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ በቀጣናው ገንቢ ሚና እየተጫወተች መሆኑንም ገልጸዋል።

ግብጽ ክፍፍልን የሚፈጥሩ፣ ሀብትን የሚያባክኑና በጋራ መልማትን የሚያሰናክሉ አካሄዶችን እየተከተለች ትገኛለች ሲሉም አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ አስታውቀዋል።
በቀጣናው ለሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች መሳሪያ በመስጠት አሉታዊ ተግባር እየፈጸመች መሆኑን አክለዋል።

"የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ተመርቋል" ያሉት አምባሳደሩ፤ ይህም ለኢትዮጵያ፣ ለናይል ተፋሰስ ሀገራትና በአፍሪካ ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ለሚሹ ሁሉ ትልቅ እርካታን የሰጠ ነው ብለዋል።

ሕዳሴ ግድብ የአይበገሬነት እና የጽናት ምልክት ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ግብጽ ኢትዮጵያ ለግድቡ ግንባታ የፋይናንስ ድጋፍ እንዳታገኝ ስትሰራ ብትቆይም ኢትዮጵያውያን በጥሪታቸውና በሀብታቸው በመገንባት ግድቡን ከፍጻሜ እንዲደርስ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ግድቡ በኢትዮጵያ እና በሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት በቀጣይ የሚገነቡ ግድቦች ጅማሮ ነው ያሉ ሲሆን፤ ይህ ለቀጣናው የጋራ ልማት ወሳኝ ሚና እንዳለው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

"የእኔ ብቻ ልጠቀም እና የአንድ ወገን የበላይነት ዘመን አብቅቷል" ያሉት አምባሳደሩ፤ ግብጽ የትብብር አማራጭን ብቻ እንድትከተል አስገንዝበዋል።

ግብጽ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤን ተጠቅማ የውሃ አጀንዳን ለጠባብ የፖለቲካ ግቦችና ለብሄራዊና ቀጣናዊ ፍላጎቶቿ ማሳኪያ እየተጠቀመች መሆኗን ገልጸው ተመድ ያለውን ስልጣን ተጠቅሞ ግብጽ ገንቢ ሚና እንድትወጣ ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

አምባሳደር ዮሴፍ ኢትዮጵያ በትብብር መንፈስ እና በጋራ የመልማት መርህ ግብጽን ጨምሮ ከየትኛውም የተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ማረጋገጣቸውን ዘገባው አመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ