ሕዳር 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የመቀሌ እና አዲግራት ዩኒቨርስቲ በትግራይ ክልል አልፎ አልፎ በሚስተዋሉ፤ የፀጥታ ስጋቶች እና በተያያዥ ገፊ ምክንያቶች ትምህርት ሚኒስቴር በ2018 ዓ.ም የመደበላቸውን የተማሪዎች ቁጥር ሙሉ በሙሉ መቀበል አለመቻላቸውን ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቀዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ያፊድ ታደሰ፤ በ2018 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር መድባ መሰረት በመደበኛው 2 ሺሕ 34 ተማሪዎች የተመደቡ ሲሆን፤ በሪሜድያል ፕሮግራም ደግሞ 624 ተማሪዎች መመደባቸውን ተናግረዋል።

በጠቅላላው ወደ ዩኒቨርስቲው ከተመደቡት 2 ሺሕ 658 ተማሪዎች መካከል፤ ወደተቋሙ ገብተው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት 2 ሺሕ 410 የሚሆኑት ናቸው ብለዋል።

ቀሪዎቹ ማለትም 248 የሚሆኑት ደግሞ፤ እስካሁን ድረስ በትምህርት ገበታቸው ላይ አልተገኙም ሲሉ አቶ ያፊድ ታደሰ ለአሐዱ ገልጸዋል።

ለዚህ ምክንያት የሆነው ደግሞ "አንዳንዶቹ ተማሪዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከፍለው መማር የሚችሉ ስለሆኑ እንዲሁም፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በቤተሰብ ጫና ምክንያት ርቀው እንዳይሄዱ ስለሚደረጉ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ጠቁመዋል።

የአዲግራት ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ገብረሚካኤል ወልደሚካኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በ2018 ዓ.ም ትምህርት ሚኒስቴር በመደበኛ 800 ተማሪዎችን እና በሪሚዲያል ፕርግራም ደግሞ 4 ሺሕ ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርስቲው እንዲገቡ መድቧል ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።

በዚህም በመደበኛው ከተመደቡት ተማሪዎች ውስጥ አብዛኛኞቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብተዋል ያሉ ሲሆን፤ በሬሚዲያል የተመደቡት ተማሪዎች ግን ሙሉ በሙሉ እስካሁን እንዳልገቡ አስታውቀዋል።

ወደ ዩኒቨርስቲው የተመደቡ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ እንዳይገቡ እንደ ገፊ ምክንያቶች የሚነሱት፤ በክልሉ አልፎ አልፎ የሚታዩ የፀጥታ ስጋት፣ የትራንስፖርት ችግር እና አንዳንዶቹ ደግሞ በግል በራሳቸው በአካባቢያቸው በሚገኙ የከፍተኛ ተቋማት የመማር ፍላጎት ስለሚኖራቸው መሆኑን የዩኒቨርስቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ለአሐዱ አስታውቀዋል።

ነገር ግን ዩኒቨርስቲዎቹ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው የነበረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና በፌደራል መንግስቱ በተደረገ ድጋፍ ጥሩ በሚባል ደረጃ ሆነው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። የሰላሙም ጉዳይ ለተማሪዎች አስጊ አይደለም ሲሉ አክለዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ