ሕዳር 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በሕጻናትና ታዳጊዎች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት በአብዛኛው የሚፈጸሙት በሕፃናቱ የቅርብ ቤተሰቦች አማካኝነት እንደሆነ ተገልጿል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባካሄደው ጥናት፤ በኢትዮጵያ በተለይም ሰላም በሌለባቸው አካባቢዎች በሕጻናትና ታዳጊዎች ላይ የሚፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች በቅርብ ቤተሰቦች እንደሚፈጸም ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶች መብት ጥበቃና ምላሽ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘካርያስ ደሳለኝ፤ ሕጻናቱ ግጭት እና አለመረጋጋት ከሚያሳድርባቸው ተጽዕኖ በተጨማሪ በቅርብ ቤተሰቦች እየተፈጸመ ያለው ጾታዊ ጥቃት አሳሳቢ እንደሆነ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
"ዕድሜያቸው ከ4 እስከ 8 ዓመት ባሉ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች በአባታቸው፣ በወንድማቸው ወይንም በአጎታቸው እንደሚፈጸም ጥናቶች አረጋግጠዋል" ብለዋል፡፡
ሕጻናትን ከአደጋ የመጠበቅና የመከላከል ኃላፊነት ያለባቸው የቅርብ ዘመዶቻቸው ራሳቸው ለሕጻናቱ ስጋት እየሆኑ መምጣታቸው አስደንጋጭ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
"በተደጋጋሚ የሚወጡ ሪፖርቶች ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መጠን እየቀነሰ ሳይሆን እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል።
በኢትዮጵያ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በዜጎችና በሀገር ላይ እያደረሱ ያሉት ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም” ያሉ ሲሆን፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ድርጊቶቹ እየተባባሱ መምጣታቸውን መሪ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም፤ የጥቃት አድራሾች ላይ አስተማሪ እርምጃዎች የመውሰድ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በሕጻናት ላይ በቅርብ ቤተሰብ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ