ሐምሌ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትምባሆ ምርት ላይ የሚለጠፉ የጤና ማስጠንቀቂያዎች ሀገራዊ ስሜት እንዲላበሱ ለማድረግ በአገራዊ ምስል የመቀየር ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ምስሎቹ ሀገራዊ መሆን የሥነ-ልቦና እና የአካባቢ ቅርበት በመፍጠር የሚያስተላለፉት መልዕክት ግቡን እንዲመታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን በባለስልጣኑ የናርኮቲክ፣ ሳይኮ ትሮፒክ እና ትምባሆ ቁጥጥር ዴስክ ኃላፊ ቶሎሳ ገመዳ ለአሐዱ ተናግረዋል።
የትንባሆ ቁጥጥር መመሪያው በሚጠይቀው መስፈርት መሠረት የትንባሆ ምርት ላይ የጤና ማስጠንቀቂያ ምስል እና ፅሁፍ እንዲኖረው የማድረግ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ኃላፊው ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት የትንባሆ ምርቶች ስዕላዊ የጤና ማስጠንቀቂያ በሀገራዊ ምስሎች እንዲተኩ ለማድረግ፤ ከኢትዮጵያ ካንሠር ማህበረሰብ፣ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
የምስሎች መቀየር ሕብረተሰቡ የምርቱን አደገኝነት እንዲገንዘብ ለማበረታታት ውጤታማ ዘዴ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
አሁን በገበያ ላይ ያሉት የትምባሆ ምርቶች ከአንድ ዓመት በኋላ ሲጠናቀቁ፤ የትንባሆ ምርት የጤና ማስጠንቀቂያዎች ምስል ሙሉ በሙሉ ሀገራዊ ምስል እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ የትንባሆ ምርት ላይ የጤና ማስጠንቀቂያ ምስልን በአገራዊ ምስል የመቀየር ሥራ መጀመሩ ተነገረ
