ሐምሌ 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት ዓመት በተደረገ ክትትል በአዲስ አበባ ከተማ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች በተለይም ለእናቶችና ሕጻናት በሚደረግ ድጋፍ ውስጥ ከ350 በላይ የሚሆኑ ዜጎች ተገቢ ያልሆነ ድጋፍ ሲያገኙ እንደነበረ ማረጋገጡን፤ የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል።

ቢሮው በተለይም ነፍሰጡር ሴቶች፣ አጥቢ እናቶችንና ሕጻናትን በተመለከተ የቀዳማይ ልጅነት እድገት ልማት ፕሮግራም ቀርፆ በርካታ ሥራዎችን እንደሚያከናውን የገለጹት፤ የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሀድጉ ፀሀዬ ናቸው።

በዚህ ሥራም በርካታ እናቶችና ሕጻናትን መደገፍ ስለመቻሉ አንስተው፤ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ላይ ሥር ሰዶ የቆየ የተረጂነት ስሜት መኖሩ ለሥራው ተግዳሮት ስለመሆኑ አስረድተዋል።

መረዳት ያለባቸውን ዜጎች ለመለየት ከብሎክ ጀምሮ በወረዳ ባለሙያዎች ከዛም ወደ ክፍለ ከተማ ተልኮ ክፍለ ከተሞች ጥናት በማድረግ ወደ ቢሮው እንደሚላክ ገልጸው፤ ይህ ሲደረግ የሚነሱ ቅሬታዎች እንደነበሩ ተናግረዋል።

ይህንንም ለመፍታት በ2017 በጀት ዓመት በተጠናከረ መልኩ ክትትል በማድረግ የማረጋገጥ ሥራ መሰራቱን የገለጹት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ በተመረጡ ቦታዎች ላይ በተሰራው ልየታ መሰረትም ወደ 359 የሚሆኑ ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ምልመላ መገኘቱን አስታውቀዋል።

"ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያትም ሥር ሰዶ የቆየው የተረጂነት ፍላጎት መቀረፍ ባለመቻሉ ነው" ብለዋል።

በመሆኑም ማህበረሰቡ ሥራው ላይ ተባባሪ በመሆን እርዳታው የበለጠ የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን መለየት እንደሚገባው ገልጸዋል።

አክለውም፤ ይህ አይነቱ ችግር አለባቸው ተብለው እንደ ስጋት የሚታዩ አካባቢዎች ላይ የመለየትና የማረጋገጡ ሥራ በደንብ እየተሰራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ይህ አይነቱ ድጋፍ መሉ ለሙሉ በከተማ አስተዳደሩ በጀት ብቻ እንደሚሸፈን ያነሱት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ ቢሮው በ2018 በጀት ዓመትም ለእናቶችና ሕጻናት የሚሰጠውን የድጋፍና ክትትል ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ