ጥቅምት 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ቢያንስ 30 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ለአእምሮ ሕመም ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል ጤና ሚኒስቴር ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።
በጤና ሚኒስቴር የአእምሮ ሕሙማን የጤና ፕሮግራም ባለሙያ የሆኑት አቶ ጀማል ተሾመ ለአሐዱ እንደገለጹት ከሆነ፤ ኢትዮጵያ ካላት 120 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ አራተኛው ወይም 30 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ በአእምሮ ሕመም እንደሚጠቃ በጥናት ተረጋግጧል።
30 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ለአዕምሮ ሕመም ተጠቂ እንዲሆን ደግሞ ግጭት፣ ጦርነት፣ ድህነት፣ የቤተሰብ ጫና፣ ፆታዊ ጥቃትና አስገዳጅ መፈናቅል ዐብይ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 500 ሺሕ የሚደርሰው ሕዝብ ለአእምሮ ሕመም የሚጋለጠው በጭንቀት ምክንያት መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡
ሆኖም መንግሥት ችግሩ እንዳይከሰት ከፌደራል እስከ ክልል ባሉት የሕክምና ተቋማት፤ የአእምሮ ሕሙማንን የሕክምና ተደራሽነትን በተገቢው መንገድ ለማረጋገጥ መዋቅራዊ አሰራር ዘርግቶ እየተሰራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 11 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ለአእምሮ ሕመም የተጋለጠ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 30 በመቶ የሚሆነውን የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ መሆኑን አሐዱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ ቢያንስ 30 ሚሊዮን ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው በአእምሮ ሕመም ሊጠቁ እንደሚችሉ ተገለጸ