ጥቅምት 30/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከጎዳና ስብከት እና ልመና ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን የእምነት አባቶች የማያስቆሙ ከሆነ፤ የሚመለከተው አካል ሕግ እንደሚያስከብር የአዲስ አበባ ከተማ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታውቋል።
እያንዳንዱ የእምነት ተቋም የራሱ የሆነ አስተምህሮ እንደመኖሩ መጠን፤ የራስን እምነት ለማስፋፋት ተብሎ የሌላውን እምነት ማንቋሸሽ ተገቢ እንዳልሆነም ጉባኤው ለአሐዱ ሬዲዮ ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ትልቅ ችግር እየፈጠረ ያለው አንዱ የሌላውን እምነት ማንቋሸሽ መሆኑን ለአሐዱ የገለጹት የጉባኤው ዋና ፀሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ፤ እነዚህ ነገሮች ወደ ውድድር፣ ፉክክር እና ጥላቻ እየተቀየሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለአብነትም የአንድን እምነት ምልክት እንዲሁም ቀኖና ማንቋሸሽና ማዋረድ እየተስተዋለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እነዚህ አካላት እምነታቸውን ሽፋን በማድረግ ይጠቀሙ እንጂ፤ የትኛውንም የእምነት ተቋማት የሚወክሉ አይደሉም ሲሉም ተናግረዋል።
ችግሩን በጊዜ መፍታት የማይቻል ከሆነ የግጭትና የጥላቻ መንስኤ ሊሆን እንደሚችልም አመላክተዋል።
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ችግሮች መለየታቸውን የተናገሩት ዋና ፀሐፊው፤ 'መጠኑ የት ቦታ ይበዛል?' የሚለውም እንደተለየ ተናግረዋል።
ቀጣዩ እርምጃ የሚሆነው ከሐይማኖት አባቶች ጋር መነጋገር መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህም በተለያዩ ጎዳናዎች ላይ የሚስተዋሉ ስብከቶች እና ሐይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ልመናዎችን ጨምሮ በሐይማኖቶች መካከል የሚታዩ የጥላቻ ንግግሮች ለማስቀረት፤ የእምነት አባቶች ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ድርጊቱ የሚቆመው በራሳቸው በእምነት አባቶች ስለመሆኑ ያነሱም ሲሆን፤ "ይህ ካልሆነ የሚመለከተው አካል ሕግ ያስከብራል" ብለዋል።
በሐይማኖቶች መካከል የሚታዩ የጥላቻ ንግግሮች መበራከታቸውን የገለጹት መጋቢ ታምራት፤ አንድን እምነት መተንኮስ፣ ማንቋሸሽ እና ማዋረድ በጣም አደገኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህንኑ ለማስቀረት በተለይም በአምስቱ የሐይማኖት ተቋማት ውስጥ ያሉ መንፈሳዊ የመገናኛ ብዙኃን የጋራ ፎረም እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
እነዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን፣ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የወንጌል አማኞች አብያተ-ክርስቲያናት ካውንስል፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን መሆናቸውን ተናግረዋል።
ፎረሙ በሰላም ዙሪያ፣ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር እና በሐይማኖቶች መካከል ያለው ትብብር የበለጠ እንዲጠናከር ያስችላል ብለዋል።
ተቋማቱ የተቋቋሙበት ዓላማ የእምነት ተቋሙን መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ እና ሞራላዊ እሴቶችን ለተከታዮች ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ያስታወሱት ዋና ፀሐፊው፤ የሰላም ዋና ሰባኪዎች መሆን እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ታማኝነት፣ እውነተኛነት እና ፍትሃዊነት ከመንፈሳዊ መገናኛ ብዙኃን የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በጎዳና ስብከት እና ልመና ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን የእምነት አባቶች ማስቆም እንደሚገባቸው ተገለጸ
"በሐይማኖቶች መካከል የሚታዩ የጥላቻ ንግግሮች ተበራክተዋል" ተብሏል