ጥቅምት 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በከተማዋ በሚገኙ ከ7 ሺሕ 900 በላይ የንግድ ተቋማት ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ወደ 323 የሚጠጉ ተቋማት እርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታውቋል።

የባለሥልጣኑ የምግብና ጤና ነክ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ እስጢፋኖስ ጌታቸው ለአሐዱ ሬዲዮ እንደገለጹት፤ ተቋማቱ ላይ እርምጃ የተወሰደው የተለያዩ የጤና ደረጃዎችን ባለሟሟላታቸው ነው።

እርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማት መካከል 262 የሚሆኑ ተቋማት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ 35 ደግሞ እንዲታሸጉ ሲደረግ፤ ወደ 20 የሚጠጉት አጫሽ ያልሆኑ ዜጎችን ከትምባሆ ጭስ ለመከላከል የወጣውን 1112/11 አዋጅ የተላለፉ ተቋማት ላይ የቅጣት እርምጃዎች መተላለፋቸውን አስታውቀዋል።

Post image

ሁለት ተቋማት ደግሞ ሥራዎች ለጤና አስጊ ሆነው በመገኘታቸው ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ እና ከገበያ እንዲወጡ ሲደረግ፤ አንድ ተቋም ደግሞ በሕግ እንዲጠየቅ ተደርጓል ነው ያሉት።

ምክንያቱን ሲያስረዱም ተቋሙ ሕገ-ወጥ እርድ በማከናወንና ሥጋ በማከፋፈል ተግባር ላይ ተሰማርቶ የተገኘ ተቋም መሆኑን ጠቁመው፤ ባለቤቱና ግብረ አበሮቹ በሕግ ተጠያቂ ሆነዋል ብለዋል።

በአጠቃላይ እነዚህ እርምጃ የተወሰደባቸው ተቋማት የምግብ፣ የጤና ነክ፣ የውበት እና የንፅህና መጠበቂያ ግብዓት አምራቾች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በአጠቃላይ ከ23 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግብና ጤና ነክ ምርቶች መወገዳቸውን አብራርተዋል።

የአዲስ ዓመት፣ የመስቀልና የኢሬቻ በዓላትን መሰረት ተደርጎ ለሚፈጠሩ ግብይቶች ደህንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ ምርቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል በከተማዋ በተካሄዱ ባዛር ቦታዎችና ተቋማት ለፍጆታ በቀረቡ ምርቶች ላይ የቁጥጥር ሥራ ባለሥልጣኑ ማካሄዱን አስታውሰዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ