ጥቅምት 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ16 ሺሕ 900 በላይ ሴቶች በጡት ካንሰር እንደሚያዙ እና ከ9 ሺሕ 600 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን ለአሐዱ እንደገለጹት፤ የዓለም ጤና ድርጅት በሚያወጣው ሪፖርት መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች በጡት ካንስር ሕመምተኛነት የሚመዘገቡ ሲሆን ከ666 ሺሕ በላይ ሴቶች ደግሞ በየዓመቱ በበሽታው ምክንያት ሕይወታቸው ያልፋል።

በኢትዮጵያ ደግሞ ከ16 ሺሕ 900 በላይ ሴቶች በጡት ካንሰር እንደሚያዙና ከ9 ሺሕ 600 በላይ የሚሆኑ በየዓመቱ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ መሪ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
እንዲሁም በዓለም አቀፍ ብሎም በኢትዮጵያ የጡት ካንሰር ሴቶችን በመግደል ቅዳሚውን ደረጃ የሚወስድ የካንሰር አይነት መሆኑን አያይዘው ገልጸዋል፡፡
በአብዛኛው የጡት ካንሰር ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም ዘግይተው ለሕክምና መምጣታቸው ሕመሙን አክሞ ለማዳን ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም ዘግይተው የሚመጡ መሆኑን ገልጸው፤ የሕክምና ውጤትን ዝቅተኛ እንደሚያደርግ እና የመኖር ዕድላቸውን እንዲቀንስ የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ታካሚዎች በጊዜ ወደ ጤና ተቋማት እንዳይሄድ በዋንኛዉ ምክንያት ሕብረተሰቡ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆንን እና ምርመራና ሕክምና የሚሰጡ የጤና ተቋማት በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸውም ለችግሩ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ችግሩን በተመለከተ የጤና ሚኒስቴር የቅድመ ምርመራ ልየታ በመጀመርያ ደረጃ ጤና ተቋማት ላይ በማሳፋት፣ ሪፈራል እና ግብረ መልስ በማጠናከር የጡት ካንሰር ውጤቱን የተሻለ ለመድርግ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
እንዲሁም የተለያዩ ካንሰር በሸታዎችን በማከም፣ መድሃኒቶችን በማቅረብ እና በርካታ የአቅም ማጎልበት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አክለዋል።
በተጨማሪም እያንዳንዱ ተቋም ምን ያህል ታካሚ እያስተናገደ እንደሆነ ክትትል በማድረግ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
አክለውም ጥቅምት ወር ሀገር አቀፍ የጡት ካንሰር የቅድመ ምርመራ ንቅናቄ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
በዚህም ዓመት "አስቀድሞ መመርመርና ሕክምናን በአግባቡ መከታተል ህይወትን ይታደጋል!" በሚል መሪ ቃል፤ በሀገራችንም ከጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ወሩን ሙሉ ይከበራል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ