ጥቅምት 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ሠንደቅ ዓላማ የተለያየ ቋንቋ እና ሐይማኖት ያለውን ሕዝብ አንድ የሚያደርግ መገለጫ ነው ሲሉ አሐዱ ያነጋገራቸው የታሪክ ምሁራን ገልጸዋል

ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአዋጅ ቁጥር 863 /2006 መሠረት በጥቅምት የመጀመሪያ ሳምንት ዕለተ ሰኞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡

18ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጲያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጲያ ሕዳሴ!” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት ተከብሯል።

አሐዱም ዕለቱን አስመልክቶ የታሪክ ምሁራንን አነጋግሯል።

በዚህም የሐይማኖትና የቋንቋ ልዩነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሠንደቅ ዓላማ አንድ ያደርጋቸዋል፤ ሠንደቅ ዓላማ አንድ የሚያደርግና የሚያስተሳስር ነው ያሉት የታሪክ ተመራማሪው በላይ ስጦታው ናቸው።

በተለያዩ የዓለም መድረኮች ኢትዮጵያን የሚወክለው ሰንደቅ አላማ ነው ያሉት አቶ በላይ በ1980ዎቹ በአትሌቲክስ ውድድር ሠንደቅ አላማን ይዘው የሚገቡት ኢትዮጵያውያን ብቻ እንደነበሩና ሌሎች ሀገራት ከኢትዮጵያ የወሰዱት ልምድ መሆኑን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ብሔራዊውን ሠንደቅ ዓላማ የሚገዳደሩ የክልል ሠንደቅ አላማዎች መኖራቸውን አንስተው፤ ቋንቋን መሠረተ ያደረገ የፌደራሊዝም ስርዓትን ማስቀረት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው አሐዱ ያነጋገራቸው የታሪክ ተመራማሪ ደረጄ ተክሌ፤ በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ላይ የይሁዳ አንበሳ መሃሉ ላይ ያለው ሆኖ ባለዘርፉ ሠንደቅ ዓላማ በቤተ-መንግሥት፣ በመከላከያ ሚኒስቴር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብቻ ሲሰቀል በሌሎች ቦታዎች ልሙጡ ሠንደቅ ዓላማ ይሰቀል እንደነበር ገልጸዋል።

ይኸው ስርዓት ቀጥሎም በደርግ መንግሥት በሠንደቅ ዓላማው ላይ ያለው አርማ ቀይሮ ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን አንስተው፤ የኢህአዴግ መንግሥት በአንፃሩ በሁሉም የሀገሪቷ ክፍል ባለኮከቡን ሠንደቅ ዓላማ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉን ጠቁመዋል።

በወቅቱ ያሉ ፖለቲከኞች በራሳቸው ፍላጎትና ለራሳቸው በሚመቻቸው መልኩ ማድረጋቸው ሠንደቅ ዓላማውን ሕዝቡ እንዳይቀበል አድርጎታል ብለዋል።

ለሠንደቅ ዓላማ የነበረው ክብር ካለፈው ትውልድ አሁን ለመጣው ትውልድ ሳይተላልፍ እንዲቀር ያደረገው ፖለቲካ እንደሆነም ያነሳሉ።

'የብሔር ብሔረሰቦች አስተዳደር ያላት ሀገር ትመሰረታለች' ተብሎ ከታወጀ በኋላ ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸው ሠንደቅ ዓላማ እንዲኖራቸው መደረጉ ጥሩ ቢሆንም፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ፈደራሊዝም ስርዓት ውቅሩ ሳይንስን መሠረት ያላደረገና በጥቂት ፖለቲከኞች ወደፊትን ያላማከለ መደረጉ ችግር መሆኑ አክለዋል።

ስለሆነም ሠንደቅ ዓላማን በደርግና በአጼ ሃይለስላሴ እንዲሁም በቀደሙት እንደበረው አሁን ባለበት አርማ ባለዘርፉን ሰንደቅ አላማ በትላልቅ ቦታዎች ላይ በማውለብለብ ልሙጡን ባንዲራ ወደ ሕዝቡ መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል።

እንዲሁም ለትውልዱ የሠንደቅ ዓላማን ክብር የሀገር መገለጫነት ለማስተማር በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ቀርጾ በማስገባት ማስተማር ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ