ሕዳር 6/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎በአይነት ሁለት የስኳር ሕመም ወይም “ታይፕ ቱ ዲያቤትስ” የሚጠቁ ሕጻናት እና ታዳጊዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የኢትዮጵያ የስኳር ሕመምተኞች ማህበር ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።

በሽታው ከዚህ በፊት በተለይም ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ በስፋት የሚከሰት ሕመም እንደነበር የገለፁት የማህበሩ ፕሬዝደንት ጌታቸው ታረቀኝ (ዶ/ር)፤ በአሁኑ ወቅት በሕጻናትና በታዳጊዎች ላይ በስፋት እየተስተዋለ ነው ብለዋል።

‎ፕሬዝደንቱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሕጻናት ላይ በብዛት የሚታየው አይነት አንድ ማለትም የኢንሱሊን መድኃኒት የሚሰጠውን ሕመም አልፈው በአይነት ሁለት የሚጠቁ ሕጻናት እና ታዳጊዎች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑን ጠቁመዋል።

‎ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሱት ደግሞ ውፍረት፣ በተለይም ሆድ አካባቢ ያለ የስብ መጠን መጨመር፣ የስኳር መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ እና የታሸጉ ምግቦችን ማዘውተር ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡

‎በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ሌሊሳ አማኑኤል በበኩላቸው፤ በዓለም ከዘጠኝ ሰው ውስጥ 7 ሰው የስኳር ሕመምተኛ እንደሆነ ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ገልጸዋል፡፡

ከነዚህም ውስጥ 81 ከመቶ የሚሆኑት ታማሚዎች የሚገኙት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት መሆኑንም ጠቁመዋል።

‎በዚህም በስኳር ህመም ምክንያት በአንድ ሰከንድ 6 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ ሲሉ ነው የገለጹት።

‎በኢትዮጵያም በዓመት 13 ሺሕ 369 ሰዎች በየዓመቱ በስኳር ሕመም ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ ተብሏል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ ካላት ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር ውስጥ 13 ነጥብ 1 ከመቶ የሚሆነው ከሕመሙ ጋር ይኖራል ሲሉ አማካሪው ገልጸዋል።

‎የስኳር ሕመም አንድ ጊዜ ከተከሰተ መዳን የማይችል ነገር ግን መቆጣጠር የሚቻል በሽታ መሆኑም አስረድተዋል።

‎የኢትዮጵያ ስኳር ሕመምተኞች ማህበር ውስጥ ታቅፈው የሚገኙ ከ20 ሺሕ በላይ ሕጻናት እና ታዳጊዎች እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን፤ የአይነት ሁለት ተጠቂዎች ቁጥርም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየጨመረ ነው ተብሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ