ሕዳር 6/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) 10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በዛሬው ዕለት በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ በደማቅ ሥነ ስርዓቶች መካሄድ ጀምሯል።

በሰመራ ስታዲየም በተደረገው የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ ፎረሙ ለከተማ መስፋፋት እና እድገት ከፍተኛ እስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

Post image

ፎረሙ "የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት" በሚል መሪ ቃል እየተከበረ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የሰመራ ሎጊያ አልሚ ባለሃብቶች ወደ ቦታው በመምጣት እንዲሰሩ የሚል ጥሪ መደረጉም ተጠቁሟል።

በተለይ አስመጭና ላኪ ባለሃብቶች ቦታው ለወደብ ቅርብ በመሆኑ ሰፊ ሥራዎች መስራት እንደሚቻል ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ለመስራት ወደ ክልሉ እንዲገቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

እስከ አሁን ክልሉ እየሰራ ባለው ልማት ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ መሆኑን በመግለጽ፤ ዘላቂ ልማትን ለማስፈን የቴክኖሎጂ አሰራር በመደገፍ ሰፊ ሥራዎችን መሰራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ፎረሙ በከተሞች ልማት፣ ዘላቂነትና መልካም አስተዳደር ዙሪያ የጋራ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሰኒ በበኩላቸው፤ የከተማ ልማት ለማረጋገጥ እኩል አካታች የሆነ አሰራር መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።

Post image

ፎረሙ በየሁለት ዓመቱ የሚከበር ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም በአፋር ክልል በሰመራ ሎጊያ ለ10ኛ ጊዜ መከናወን ጀምሯል ብለዋል።

በተለይ የከተማ ልማትን ለማዘመን ተቋማዊ አደረጃጀትና ዲጂታላይዜሽን በማስፋት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

እንዲሁም የከተማ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማረጋገጥ፣ የከተሞች ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና የተፈጠነ አገልግሎትን ለማረጋገጥ ብሎም በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተሞችን መመስረት ፎረሙ ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለው ተናግረዋል።

Post image

አፋር ክልል ይህንን ትልቅ ሀገራዊ ክስተት በማስተናገዱ ከፍተኛ ኩራት የሚሰማው መሆኑን ገልጿል።

በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ኡመድ፣ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ከተለያዩ ከተሞች የመጡ እንግዶች ተገኝተዋል።

Post image


ዛሬ ማለትም ሕዳር 6 ቀን 2018 ዓ ም በይፋ የተጀመረው ይህ የከተሞች ፎረም እስከ ሕዳር 10 ቀን 2018 ዓ ም የሚካሔድ ሲሆን፤ የጎረቤት ሀገራት ከጅቡት እና ሶማሊ ላንድ ከተሞችን ጨምሮ ከ150 በላይ ከተሞች እንዲሁም ከ10 በላይ የንግድ ድርጅቶች ተሳትፈውበታል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ