ሕዳር 6/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የውጭ ዜጎች አካላዊ ጥቃትና እገታ እንደተፈመባቸው የሚናገሩት ሆን ብለው የከተማዋን ገፅታ ለማበላሸት ነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቱሪዝም ኮሚሽን ገለጸ።

ከሰሞኑ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ መዲናዋ ከመጡ ወዲህ በከተማዋ በነበራቸው ቆይታ ወቅት በተለያዩ አካላት የአካላዊ ጥቃትና የእገታ ወንጀል እንደተፈጸመባቸው በማኅበራዊ ትስስር ገፆቻቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

አሐዱም ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቱሪዝም ኮሚሽንን አነጋግሯል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ በሰጡት ምላሽ፤ "የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያ ከመጡ ወዲህ የእገታ ወንጀል እና አካላዊ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው በማስመሰል በማኅበራዊ ሚዲያዎች መረጃዎችን የሚያሰራጩት የሀገራችንን እና የከተማዋን ገፅታ ለማበላሸት ሆን ብለው ነው" ሲሉ አብራርተዋል።

Post image

እንዲሁም በማኅበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ግርታን በመፍጠር ተከታይ ለማፍራት እንደሆነ የገለጺ ሲሆን፤ መሰል ድርጊቶች በሀገር ገፅታ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር እንደሚፈጸሙ ጠቁመዋል።

ከተማዋን ለመጎብኘት የሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች የሚኖራቸውን ቆይታ አጠናቅቀው ወደየ ሀገሮቻቸው እስኪመለሱ ድረስ ጥበቃ እና ከለላ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል።

ሀሰተኛ መረጃዎች በተገለጹት አካላት መረጃው ከተሰራጨ ወዲህ፤ በሕዝብ ዘንድ ግርታ እንዳይፈጠር የማጣራት ሥራ የሚመለከታቸው አካላት መስራታቸውን አድንቀዋል።

መሰል ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ትክክለኛ መረጃዎችን ለሕዝብ ለማድረስ በቅንጅት ሥራዎች እንደሚሰሩ ያሳሰቡት ኮሚሽነሩ፤ ኢትዮጵያ ከእንግዳ አቀባበል ጋር በተያያዘ ያላቸው ምግባር መሰል ተግባራትን እንዳይፈፅሙ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የቱሪዝም ዘርፍ በአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን ድርሻ ለማሳደግ ነባርና አዳዲስ የመዳረሻ ልማቶችን ማካሄድ፣ የመስህብ ሀብቶችን ማስተዋወቅ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት የሚመጥን መዋቅራዊ አደረጃጀትና የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አሠራር መዘርጋትም ሌላው ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ይጠቁማሉ።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ