ጥቅምት 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ውስጥ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት በየሰዓቱ 25 ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከእነዚህም መካከል ካንሰር 17 በመቶውን፣ ስኳር 12 በመቶውን፣ ስር የሰደደ የመተንፈሻ አካላት በሽታ 7 በመቶውን ይይዛሉ ተብሏል፡፡
በዓመት በአጠቃላይ 43 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች በዚህ ዓይነት በሽታዎች ምክንያት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ቡድን መሪ ሙሴ ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ቡድን መሪው በማብራሪያቸው፤ "በቅድመ መከላከል ልንቆጣጠረው የምንችለው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት ከ100 ሺሕ ሰዎች መካከል 554ቱን በዓመት ይገድላል" ብለዋል።
በተለይ ለልብ እና የደም ስር በሽታዎች የሚታዘዙ መድኃኒቶችን እጥረት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተው፤ በሽታዎቹ የእድሜ ልክ መድኃኒት መውሰድ እና ጥንቃቄ የሚጠይቁ በመሆናቸው ታካሚዎች ለከፍተኛ ስነ-ልቦና ችግር የሚዳረጉበት አጋጣሚ እንለም ተናግረዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የቅርብ ጊዜ ጥናት 80 ከመቶ የሚሆኑ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል ይቻላል ማለቱን ያነሱት ቡድን መሪው ዶ/ር ሙሴ፤ ሚኒስቴሩ ጤና ሚኒስቴር የበሽታዎችን ስርጭት ለመቀነስ ግንዛቤ የሚሰጡ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከባለሙያዎች በተጨማሪ መገናኛ ብዙኃንን እና ማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ በሰዓት 25 ሰዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ሕይወታቸው ያልፋል ተባለ
80 ከመቶዎቹን በሽታዎች መከላከል ይቻላል ተብሏል