ጥቅምት 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሁሉም ባንኮች የግል ባንክ ሂሳቦችን ለንግድ እና ለሕገ-ወጥ ድርጊት የሚጠቀሙ ደንበኞችን አስመልክቶ አስፈላጊ መረጃዎችን በማደራጀት እንዲልኩ መመሪያ አስተላልፏል፡፡

ብሔራዊ ባንክ አደረኩት ባለው ምርመራ "ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የባንክ ደንበኞች በዋናነት የንግድ ድርጅቶችና ግለሰብ ነጋዴዎች ለንግድ ሥራቸው ተብሎ ከተከፈተው እና በሚመለከተው የግብር ሰብሳቢ ተቋም ካስመዘገቡት የባንክ ሒሳቦች ውጭ የግል የባንክ ሂሳባቸው ወይም የሶስተኛ ወገን የባንክ ሒሳብ ተጠቅመው የተለያዩ የንግድ ግብይቶች እና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች እየፈጸሙ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ" ብሏል።

Post image

ይህ አሰራር ከግብር ሰብሳቢ ባለስልጣናት ቁጥጥርና ክትትል ለመሸሽ የሚደረግ ተግባር ከመሆኑ በተጨማሪ፤ በዚህ አግባብ የሚፈጸሙ የፋይናንስ ግብይቶች እና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች የወንጀል ፍሬ ወይም ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ጋር የተያያዙ ወይም የተገናኙ ሊሆኑ ይችላሉ ሲልም ገልጿል።

በዚህም መሠረት እነዚህን መሰል ተግባራትን ለመግታት አስፈላጊው የተቀናጀ እርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑን አስታውቋል።

የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤናማነትና ታማኝነት እንዲሁም በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ደህንነት ለመጠበቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሁሉም ባንኮች የግል ባንክ ሂሳቦችን ለንግድ እና ለሕገ-ወጥ ድርጊት የሚጠቀሙ ደንበኞችን አስመልክቶ አስፈላጊ መረጃዎችን በማደራጀት እንዲልኩ መመሪያ አስተላልፏል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ