ጥቅምት 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሕንድ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው የካርናታካ ግዛት ዋና ከተማ ቤንጋሉሩ፤ አንድ የትራፊክ ፖሊስ በመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ሾፌሩን በጥፊ ሲመታ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መሰራጨቱ ከፍተኛ ሕዝባዊ ቁጣ አስነስቷል።
"በአደባባይ የተፈጸመ አካላዊ ጥቃት" በሚል የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ቁጣ የቀሰቀሰው የትራፊክ ፖሊሱ ድርጊት የተፈጸመው በሼል ነዳጅ ማደያ አቅራቢያ ሲሆን፤ ሾፌሩ በተከለከለ ስፍራ ለ5 ደቂቃ መኪናውን አቁሞ እንደነበር ተገልጿል።
ይህ ክስተት በተንቀሳቃሽ ምስል የተቀረጸው በአካባቢው በነበረ አንድ መንገደኛ ሲሆን፤ የትራፊክ መኮንኑ ወደ ሾፌሩ ቀርቦ በቁጣ ከጮኸ በኋላ ሹፌሩን በጥፊ ሲመታው በተንቀሳቃሽ ምስሉ ታይቷል፡፡
የፖሊስ መኮንኑን ድርጊት በጽኑ ያወገዙት የማኅበራዊ ትስስር ተጠቃሚዎቹ ድርጊቱን "ስልጣንን አለአግባብ መጠቀም" ያሉት ሲሆን፤ ሾፌሩ ተሸርካሪውን የተከለከለ ቦታ ላይ ማቆሙ ስህተት ቢሆንም የፖሊስ መኮንኑ የወሰደው እርምጃ ግን ከሕግና ከሥነ-ምግባር ውጭ ነው ብለዋል።

በርካቶችም መንግሥት በጥፋተኛው ፖሊስ ላይ ፈጣን እና ተመጣጣኝ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሌላ የትራፊክ ፖሊስ አሽከርካሪን በጥፊ በመምታቱ የሕዝብ ቁጣ የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ በኋላም ትራፊኩ ከሥራ ታግዷል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ