ሕዳር 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከአዲስ አበባ የግብር አሰባሰብና የገቢዎች አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚኖረውን ማንኛውም አይነት ቅሬታ መፍታት የሚያስችል አዲስ አሰራር በከንቲባ ፅ/ቤት ሥር መዋቀሩ ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ ሥር የተዘረጋው የቅሬታ አፈታት ስርዓት እንደተጠበቀ ሆኖ በዚያ ያልረካ ግብር ከፋይ ከንቲባ ፅ/ቤት ማንኛዉንም አይነት ከገቢ አሰባሰብ፣ ከሠራተኞች ሥነ-ምግባር እና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚነሱ የግብር ከፋዮች ቅሬታዎችን ለመፍታት ዘወትር ሐሙስ ኃላፊዎች በተገኙበት የሚደመጥ እና ተጣርቶ ምላሽ የሚሰጥበትን አሰራር መዘርጋቱን ነው የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ፅ/ቤት ያስታወቀው።

በዚህም መሠረት በሚስጥር ጥቆማ የሚሰጥበትን ነፃ የጥሪ ማዕከል 9977 ፣ የሚስጥር ሳጥንን ጨምሮ በተጨባጭ ቅሬታዉን በአካል ለበላይ አመራር ማቅረብ የሚችልበትን አሰራር ወደ ተግባር ይገባል ተብሏል።

በመሆኑም ከመጪው ሐሙስ ሕዳር 25 ቀን 2018 ጀምሮ ጠዋት ከ 2 ሰዓት እስከ 7 ሰአት ድረስ ከገቢዎች ጋር ብቻ የተያያዘን ቅሬታ አመራሩ ተቀብሎ የሚስተናግድ መሆኑን በመረዳት፤ በከንቲባ ፅ/ቤት ተጨባጭ ቅሬታ ያላቸው ግብር ከፋዮች ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ