ጥቅምት 7/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል ከጦርነቱ በፊት የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት ከ1 ነጥብ 4 በመቶ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን ወደ 4 ነጥብ 4 መቶ ከፍ ማለቱን የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ (ዶ/ር) አማኑኤል ሃይለ ለአሐዱ እንደተናገሩት ከሆነ፤ በክልሉ ከጦርነቱ በኋላ ዜጎች የቫይረሱ ስርጭት ማሻቀብ በተጨማሪ በቂ የሆነ የሕክምና ክትትል ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል።

"የሰሜኑ ጦርነት የትግራይን ክልልን የጤና መሠረተ ልማት በእጅጉ የጎዳ ነበር" ያሉት የጤና ቢሮ ኃላፊው፤ ይህም ዜጎች ለተለያዩ ወረርሽኞችና ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ እንዲጋለጡ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ ከጦርነቱ በኋላ በተለየ ሁኔታ ከ6 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ከከተማ እስከ ገጠር ልየታ በማድረግ በተደረገ ጥናት በተገኘ ውጤት፤ የኤች አይቪ ኤድስ በሽታ ስርጭት ወደ 4 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ማለቱ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ለዚህም በጦርነቱ ወቅት ብዛት ያለው ወታደር ከከተማ እስከ ገጠር ባሉት የትግራይ ዞኖችና ወረዳዎች መግባቱ፣ የተፈናቃይ ቁጥር መጨመሩ፣ በቂ የሆነ የበሽታ መከላከያ፣ የሕክምና መሳሪያና የመድኃኒት አቅርቦት አለመኖር እንዲሁም፤ ለሁለት ዓመት ያህል በክልሉ የሚገኙ ዜጎች ደመወዝ ተቋርጦ መቆየቱ አሁን ለሚታየው የቫይረሱ ስርጭት ዋነኛ ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ተናግረዋል።

"አንድ ሰው በኤች አይቪ የተያዘው መቼ ነው? እንዲሁም ቫይረሱ ወደ ደሙ መቼ ነው የገባው? የሚሉትን ቀነ ገደቦች ማጤን ያስፈልጋል" ያሉት ኃላፊው፤ በዚህ የምርመራ ሂደት ደግሞ በክልሉ ያለው የበሽታው ስርጭት አሁንም መጨመሩን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ከጦርነቱ በፊት 46 ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች በኤች አይቪ ቫይረሱ ተይዘው እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር አማኑኤል፤ በአሁኑ ወቅት የሕክምና መድኃኒታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ ያሉት 37 ሺሕ ብቻ ናቸው ብለዋል።

ቀሪዎቹ ማለትም 9 ሺሕ የሚሆኑት ተጠቂዎች በሕይወት ስለመኖራቸው የሚታወቅ ነገር የለም ሲሉም ኃላፊው ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ