ጥቅምት 7/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከሚጠፉ ግለሠቦች የአፋልጉኝ ማስታወቂያዎች ላይ ስልክ ቁጥሮችን በመውሰድ ገንዘብ አስገቡ በሚሉ ግለሠቦች ላይ ጥብቅ ምርመራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።
በተለያዩ ጊዜያት ከቤተሰቦቻቸው የሚጠፉ ሕጻናት፣ ታዳጊዎችና ጎልማሶች ወላጆቻቸው፣ አሳዳጊዎቻቸው ወይም ቤተሰቦቻቸው ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ከመውሰድ ይልቅ በተለያዩ መንገዶች የአፋልጉኝ ማስታወቂያዎችን እንደሚለቁ ይታወቃል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚለቀቁ የአፋልጉኝ ማስታወቂያዎች ላይ ከሚጠፉ ግለሰቦች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው አንዳንድ ግለሰቦች "ልጃችሁ ወይም የጠፋው ሰው እኛ ጋ ነው ገንዘብ አስገቡ፤ ይህን ካላደረጋችሁ በህይወት አታገኟቸውም" በማለት በርካታ ገንዘብ በባንክ እንዲገባላቸው ያደረጉ ግለሰቦች ላይ ፖሊስ በጥናት የተደገፈ የወንጀል ምርመራ ተግባር መጀመሩን አስታውቋል።
ወላጅ የልጁን ወይም የቤተሰብ አባሉን መጥፋት ለፖሊስ ካሳወቀም 'ሊሞቱብን ይችላሉ' በሚል ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ይዞ ከመምጣት ይልቅ ገንዘብ ለጠየቁ፣ በዚህ የወንጀል ተግባር ላይ ለተሠማሩና ለተደራጁ ወንጀል ፈጻሚዎች ገንዘብ እያስገባ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እየተጋለጠ እንደሚገኝ እየተደረጉ ባሉ የምርመራ ሥራዎች መረጋገጡን ገልጿል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ መሰል ወንጀሎች የሚፈጽሙ ግለሰቦችን አስመልክቶ በተደጋጋሚ አቤቱታዎች እንደሚቀርቡልት የተለያዩ የወንጀል አፈጻጸሞችን ለአብነት በማቅረብ የገለጸ ሲሆን፤ አቤቱታዎችን ተቀብሎ ተገቢውን ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡
በዚህም ገንዘብ እንዲገባላቸው የጠየቁ፣ ገንዘብ የገባላቸውና ከዚህ ወንጀል ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ላይ ጥብቅ ምርመራ መጀመሩን ገልጿል።
ሕብረተሰቡ አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ ችግሮች ሲያጋጥሙት ጉዳዩን ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ከማምጣት ይልቅ ሕግን ተከትሎ ለፖሊስ በማመልከትና ምርመራ እንዲጀመር በማድረግ ራሱን ከወንጀል ፈጻሚዎች እንዲጠብቅ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን አስተላልፋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ፖሊስ ከሚጠፉ ግለሠቦች የአፋልጉኝ ማስታወቂያዎች ላይ ስልክ ቁጥሮችን በመውሰድ 'ገንዘብ አስገቡ' በሚሉ ግለሠቦች ላይ ጥብቅ ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ
