ለኢትዮጵያ ትክክለኛ ተቆርቋሪ ዲያስፖራ በምክክር ሂደቱ የተሳተፈው ነው? ወይስ በደጅ ሆኖ የተቃወመው ነው? የሚለው አጠያያቂ ነው ሲል የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡
ኮሚሽኑ ምክክር ባደረገባቸው አዳራሾች ከ200 እስከ 300 ሰዎች በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሲሳተፉ 10 እና 20 የሚሆኑት ደግሞ ደጅ ሆነው ታቃውሞ አሰምተዋል ሲል በዛሬው ዕለት መግለጫው አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በትግራይ ክልል እስከ ጥቅምት አጋማሽ የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሊደርግ የሚችለበት ዕድል እንዳለም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ ከማሰባሰብና ተወካዮችን ከማስመረጥ አኳያ ቀሪው ዋና ሥራ በትግራይ ክልል መከናወን ያለበት ተግባር መሆኑን አስታውቋል፡፡
የምክክሩን ሂደት በትግራይ ለማስጀመር አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች መቀጠላቸውም ነው የተገለጸው፡፡
በትግራይ ክልል ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በሁለት ዙር በተደረጉ ውይይቶች የተገኙ ግብዓቶችን መሠረት በማድረግ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ ያነሳል፡፡
ከፌደራል መንግሥት ጋር በተያያዘ የተነሱ ጉዳዮችን በተመለከተም ኮሚሽኑ ለፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጉዳዮቹን ማቅረቡን በዛሬው ዕለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልጿል፡፡
ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ሌ/ጀነራል ታደሰ ወረደ ጋርም ውይይቶች ተደርገዋል ተብሏል፡፡
በጊዜያዊ ፕሬዝደንቱ በኩል ጥቅምት አጋማሽ አከባቢ ወደ ሥራ ሊጋባ የሚችልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ተስፋ መሰጠቱንም የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል አሁን ያለበት ሁኔታ ምክክር ለማድረግ አስቻይ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ግዜ በክልሉ የሚገኙ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ የተሰዘረውን ህወሓትን ጨምሮ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡
ለዚህም እንደ ምክነያት የሚያነሱት ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን ያላነሱ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው የሚል ነው፡፡
ሌላው "የትግራይ ግዛታዊ አንድነት በተጣሰበት ሁኔታ ምክክር ማድረግ ፋይዳው ምንድን ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
ይሁን ኮሚሽኑ አሁንም በትግራይ ክልል አጀንዳ ለመሰብሰብ ፍላጎት እንዳለውና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ፌደራል መንግሥት እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲፈቱ ይጠይቃል፡፡
ይሁን እንጂ እስካሁን ባለው አጀንዳ ለመሰብሰብም ሆነ ተሳታፊ ልየታ ለማድረግ የሚያስችል እንስቃሴ አልጀመርም፡፡
ይህ በሆነበት ሁኔታ ግን ኮሚሽን ከጊዜያዊ አስተዳደሩ በጥቅምት አጋማሽ ወደ ሥራ ሊገባ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
በትግራይ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ ለማከናወን ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ሙከራ ሲደርግ መቆየቱን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
በዚህ መሠረትም በፌደራል መንግሥቱ እና ጊዜያዊ አስተዳዳሩ ውይይት ካከናወኑ በኃላ ውሳኔያቸው የሚጠበቅ መሆኑን ገለጹ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ከዚህ በላይ አቅም እንዳሌለውም አንስተዋል፡፡
"በትግራይ ክልል የሚደረገው የምክክር ሂደት እንደ ሌሎች ክልሎች እንዳለሆነ ኮሚሽኑ ይገነዘባል" ሲሉም አቶ ጥበቡ ይናገሉ፡፡
በዚህም ምክንያት የተለየ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያነሱ ሲሆን፤ ችግሮችን ተቋቁሞ ምክክር ማደረግ አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡
በዋናነትም ዘላቂ የሆነ ሰላም እና መረጋጋት ብሎም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል መተማመንን ለመፍጠር የኮሚሽኑ ሥራ ላቅ ያለ መሆኑም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር በሦስት ሁነቶች የሚካሄድ መሆኑ የሚገለፅ ሲሆን፤ አንደኛው በግጭት ውስጥ የሚካሄድ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
ኮምሽኑም ለዚህም ጥሩ ማሳያ በሚል በየመን የተካሄደው ሙከራ የሚያነሳ ሲሆን፤ ሂደቱ ግን አለመሳካቱን ያነሳል፡፡
ቃል አባዩ አቶ ጥበቡ ታደሠ "በተለያዩ ሂደቶች ውስጥ የሚካሄዱ ምክክር እንደተሞክሮ ቢወሰድም፤ የኢትዮጵያ ምክክር በተመሳሳይ መንገድ ይቀጥላል ማለት አይደለም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክር ከግጭት እንደወጡ የሚያካሂዱት መሆኑም የሚነሳ ሲሆን፤ ለዚህ እንደ ማሳያ ደግሞ ቱኒዚያ ትጠቀሳለች፡፡
ቱኒዚያ በዓረብ አብዮት ብዙ ቀውሶች ከተፈጠሩና ሀገሪቱ መንግሥት አልባ ከሆነች በኋላ ሕዝቦቿ ተሳባስበው ምክክር አድርገው ሀገራቸውን ማዳን ችለዋል፡፡
ሌላው ግጭት ውስጥ ሳይገባ ምክክር ማድረግ የሚቻልበት ሒደት መሆኑ የሚነሳ ሲሆን፤ በሁሉም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ምክክር የሚያካሂዱ ሀገራት ከሚታየው የአካልና የቁስ ጉዳት ባለፈ ለትውልድ የአዕምሮ ስብራትን ለመጠገን የሚያከናውኑት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች ያሉ ታጣቂዎች ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ብዙ ጥረቶች እና ጥሪዎች ቢቀርቡም ለውይይቱ የቀረበ አለመኖሩን ኮሚሽኑ ያነሳል፡፡
ኮሚሽኑ በአማራ ክልል እንዲሁም በኦሮሚያ እና መንግሥትን ጨምሮ ወደ ውይይት እንዲመጡ ጥሪ እያቀረበ መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በስዊዲን እና በእንግሊዝ ዲያስፖራ ማህበረሰቦችን አጀንዳ ማሰባሰብ ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ወደ አጀንዳ አሰባሰቡ ከመገባቱ በፊትም ተሳታፊዎቹ ስለ ምክክር መሠረታዊ ጉዳዮች፣ ኮሚሸኑ ስላከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት እንዲሁም፤ ሂደቱን በገለልተኝነትና በነጻነት ለማካሄድ ያለውን አሰራር በተመለከተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማደረጉንም አስታውቋል፡፡
ተሳታፊዎቹ በመድረኮቹ ለመሳተፍ ፍቃደኛ የሆኑ ግለሰቦች የተለያዩ የማህበረሰብ/ ኮሚኒቲ አደረጃጀት ተወካዮች፣ ወጣቶች ሴቶች እና ሌሎችም ናቸው፡፡
አጀንዳቸውን ከመስጠታቻው በተጨማሪም በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችንም መርጠዋል፡፡
አቶ ጥበቡ ታደሠ ምክክሩ በተለያዩ ሁኔታ ሲቃወሙ የነበሩ የዲያስፖራ አባላት ወደ ምክክር እንዲገቡ ተደጋጋሚ ጥሪ እንደተደረጋለቸው ገልጸው፤ "ነገር ግን ፍቃደኛ መሆን አልቻሉም" ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ማስተላለፍ የሚፈልጉትን ሀሳብ ወደ አዳራሾ በመግባት ሀሳባቸውን ማስተላለፍ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ ጥበቡ "ለኢትዮጵያ ትክክለኛ ተቆርቋሪ ዲያስፖራ የትኛውን በምክክር ሂደቱ የተሳተፈው ነው? ወይስ በደጅ ሆኖ የተቃወመው ነው? የሚለው አጠያያቂ ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ኮሚሽኑ በአካል ባልደረሰባቸው ሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በበይነ መረብ በመታገዝ አጀንዳቸውን እንዲሰጡና ተወካዮቻቸውን እንዲመርጡ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ኮሚሽኑ በቀሪው ስድስት ወር ያነሰ ጊዜ እንዳለው ያነሱም ሲሆን፤ በቀሪ ሥራዎች የትግራይ ክልል በምክክሩ የማሳተፍ ሥራውን የማጠናቀቅ ሥራ ይሰራል ብለዋል፡፡
"ይህ ማለት ግን ለይስሙላ ለማሳተፍ የታለመ ሳይሆን በሀገራቸው ጉዳይ ስለሚመለከታቸውና መሳተፍ ስለሚገባቸው ነው" ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከሕዝባዊ መድረኮችና በልዩ ልዩ መንገዶች የተሰባሰቡ አጀንዳዎችን የማደራጀትና የማጠናቀር እንዲሁም፤ ለምክክር ጉባዔው አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን ለማጠናቀቅ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም የአጀንዳ ቀረጻ እና የምክክር ጉባዔው የሚካሄድባቸውን የአሰራር ሥርዓቶችንና ዝርዝር የማስፈጸሚያ እቅዶችን የማዘጋጀት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ተነስቷል፡፡