ጥቅምት 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በተለያዩ አማራጭ የሕጻናት ክብካቤ እና ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ውስጥ አድገው 18 ዓመት ከሞላቸው በኋላ የሚወጡ ወጣቶች ወደ ማሕበረሰቡ ሲቀላቀሉ የተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋጥማቸው ተገልጿል፡፡

ከአማራጭ ሕጻናት ክብካቤ እና ድጋፍ አድገው የወጡ ወጣቶች ማህበራት ጥምረት ከኤስ ኦኤስ የህፃናት መንደሮች በኢትዮጵያና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ያዘጋጀው የመጀመሪያው "የኢትዮጵያ ኬር ሊቨርስ ቀን" በዛሬው ዕለት ተከብሯል።

Post image

መድረኩ በኢትዮጵያ አማራጭ ህፃናት ክብካቤ እና ድጋፍ አድገው የወጡ ወጣቶች ያለፉትን የማይታመን ጥንካሬ፣ ብርታት እና ያልተገደበ አቅም ለማክበር በማሰብ የተዘጋጀ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ኬር ሊቨርስ ቀን ላይ "ያለፈ ታሪካችን የወደፊት ሕይወታችንን አይወስነውም ይልቁንም ያበረታናል" በሚል መሪ ቃል የተለያዩ የፓናል ውይይቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በዚህም መድረክ ላይ 18 ዓመት ሞልቷቸው ከአማራጭ ሕጻናት ክብካቤ እና ድጋፍ አድገው የሚወጡ ወጣቶች፤ ባሳለፉት አለመረጋጋት ጥልቅ የሆነ የአእምሮ ጤና ጉዳቶችን ይዘው እንዲያድጉ እንደሚያደርጋቸው ተመላክቷል፡፡

‎በተጨማሪም ከአማራጭ ክብካቤና ድጋፍ የሚወጡ ወጣቶች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ፤ መታወቂያ ያለማገኘት፣ የሥራ እድል አለማገኘት፣ ማህበራዊ ችግር እንዲሁም ማህበረሰቡ በወጣቶች ላይ ያለው አመለካከት የተስተካከለ አለመሆን ትልቅ ተግዳሮት እንደሚሆንባቸው ጥምረቱ አስታውቋል፡፡

Post image

በዚህም 18 ዓመት የሞላቸው ወጣቶች ከአማራጭ ድጋፍና ክብካቤ ተቋም መውጣት ዙሪያ የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ላይ ባለመካተቱ እስካሁን ብዙዎቹ ለችግር እንደሚጋለጡ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህንን እና ሌሎች ችግሮችን ለማስቀረት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተነግሯል።

‎ብሔራዊ አማራጭ የሕጻናት ክብካቤ ጥምረት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ዕድሜ የሆናቸው ህፃናትን ያካተተ ሲሆን፤ ለ3 ዓመት ከ6 ወር የሚቆይ ፕሮጀክት እንደሆነ ተገልጿል።

‎ጥምረቱ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ከቤተሰብ ውጪ ከሕጻንነታቸው ጀምሮ በተለያየ ክብካቤ አማራጭ እየኖሩ ላሉ እና በማሳደጊያ ውስጥ ላለፋ ሕጻናት ጥቅማቸው፣ መብታቸው እና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የሚሰራ ነው ተብሏል።

‎ጥምረቱ "ኤስ ኦ ኤስ አልሙናይ ወጣቶች ማህበር"፣ "ሠላም ፍሩትስ ማህበር" እና የ"ኬር ሊቨርስ በጎ አድራጎት ማህበር" ጥምረት ሲሆን፤ በማዕከሉ አድገው የወጡ ወጣቶች የመሰረቱት ማህበር መሆኑን፤ የኤስ ኦ ኤስ አልሙናይ ወጣቶች ማህበር በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ጌታቸው ለአሐዱ ራዲዮ ተናግረዋል።

‎ዳይሬክተሩ አክለውም፤ በየማዕከሉ አድገው ከማዕከሉ የሚወጡ ወጣቶች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ እንዳይገለሉና ማግኘት ያለባቸውን ጥቅምና መብት እንዲያገኙ የሚሰራ ጥምረት ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት የተከናወነው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኬርሊቨርስ ቀን ታላቅ ተስፋን የሚያስቀጥል፣ ጥልቅ ግንኙነቶችን የሚያነሳ እንዲሁም፤ ሁሉም በአማራጭ ሕጻናት ክብካቤ እና ድጋፍ ያለፈው ሰው ስኬታማ የሚሆንበትን የወደፊት ጊዜ መንገድ የሚከፍት መሆኑ ተነግሯል።

ጥምረቱ በብሔራዊ አማራጭ የሕጻናት ክብካቤ አድገው የወጡ ማህበራት ጥምረት ከሐምሌ 2016 ዓ.ም በኢፌድሪ ሲቨል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በምዝገባ ቁጥር 7316 ፍቃድ አግኝቶ ሥራ መጀመሩ ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ