ጥቅምት 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) አካል ጉዳተኞችን በሁሉም ዘርፎች እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ በተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር ለ8ተኛ ጊዜ የግብዓት ማሰባሰብ ውይይት ትናንት መስከረም 30 ቀን 2018 ተደርጓል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ በመድረኩ እንደገለጹት፤ ይህ ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲ ሲዘጋጅ ሰፊ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተደርጎበታል፡፡

Post image

በዋናነትም የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑት ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራትንና የክልል የአካል ጉዳተኞች ማህበራት፣ ከሁሉም የፌዴራልና የክልል አስፈጻሚ ተቋማት የተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና የማህበራዊና የስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች፣ በሁሉም ክልሎች ከሚገኙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይና የፍትህ ጉዳይ ቢሮዎች የሥራ ኃላፊዎች 'በረቂቅ ፖሊሲው ውስጥ ሊካተቱ ይገባቸዋል' ያሏቸውን ጠቃሚ ግብዓቶች አንስተዋል፡፡

በተለይም አካል ጉዳተኞች ክብራቸው፣ መብታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ፤ በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጉዳዮች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ በመሆኑ፤ ይህ ፖሊሲ በሕግ ደረጃ ጸድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ለማድረግ የታሰበ መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታዋ ገልጸዋል።

Post image

በረቂቅ ፖሊሲው እንዲካተቱ የተደረጉ ዋና ዋና ጉዳዮችና አቅጣጫዎች አካል ጉዳትን መከላከል ተሃድሶና መልሶ ማቋቋም፣ የጤና ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሆኑ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ የሚያደርጉ የአሰራር ስርዓቶችን መዘርጋት፣ አካል ጉዳተኞች ራሳቸውን እንዲችሉና በሀገሪቱ ልማት ውስጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ያለምንም መድሎና መገለል የሥራ እድል እንዲሁም በቂ ክህሎት እና ልምድ እንዲያገኙ ማድረግ የመሳሰሉ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ አንስተዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ