ጥቅምት 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በቀጣይ የትምህርት ዘመን ሚኒስቴሩ ተማሪዎችን ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደማይመድብ፤ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታውቀዋል።
የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተልዕኮን እንዲተገበር እና የተቋማቱን አዳዲስ መለኪያን የያዘ ሁለተኛው የፊርማ ሥነ-ስርዓት በከፍኛ የጥምህርት ተቋማት እና በትምህርት ሚኒስቴር መካከል ተካሂዷል፡፡
በዚህ የፊርማ ሥነ-ስርዓት ላይ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊዎችና የሁሉም ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች ተገኝተዋል።
በዚህም የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን ቀርጾ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትምህርት ዘመኑ በእቅድ የሚያከናውኗቸውን ቁልፍ ተግባራት አፈጻጸም በመከታተል ለሚከሰቱ ክፍተቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግና ተጠያቂነትን ማስፈን ተጠቃሽ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ መድረክ ላይ፤ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምደባ ሳይሆን በተማሪዎች ምርጫ እንዲሆን ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥራት ያለው ተማሪ ከማፍራት እና የጥናትና ምርምር ውጤት ከማቅረብ ረገድ ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም አዲስ አሰራር 'የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምን ያህል በተማሪዎች ተመራጭ ናቸው' የሚለው በትኩረት የሚታይ ነው ብለዋል።
የሥራ ዕድልን ከመፍጠር፣ ጥሩ ክፍያን ከማስገኘት፣ የትምህርት ዘርፍ፣ የትምህርት ጥራት ከማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ተቀዳሚ ምርጫ ለመሆን ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
ተማሪዎችን ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በፍላጎታቸው ማስገባት ዩኒቨርስቲዎችን ስጋት ውስጥ የሚጥል መሆኑንም፤ ፕሮፌሰሩ በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ወቅት ተናግረዋል።
በተያያዘ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች እና የሥራ ኃላፊዎች የተማሪዎቻቸውን ትክክለኛ መረጃ ካላቀረቡ ከኃላፊነታቸው የሚነሱ መሆኑ ተነግሯል።
በዚህም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስለ ተማሪያቸውና አጠቃላይ የትምህርት ስርዓት አፈጻጸም ትክክለኛ መረጃን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካላቀረቡ፤ የዩኒቨርስቲን ፕሬዚዳንቶች ጨምሮ አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንደሚነሱ ተገልጿል።
በ2018 የትምህርት ዘመን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተማሪያቸውን ትክክለኛ መረጃ የማቅረብ ግዴታ ተፈፃሚ እንደሚሆን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፤ ይህም በቀጣይ 6 ወራት ይተገበራል ብለዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ በበኩላቸው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መለኪያና የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ የሚያስችለው ስምምነት ከፍተኛ የትምህር ተቋማትን አቅጣጫ ለማስያዝ በማለም በባለፈው ዓመት የተጀመረ ስለመሆኑ አስታውሰዋል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ የተከናወነው ይህ የከፍተኛ ተቋማት እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስምምነት ቀጣይነት እንደሚኖረውም አስታውቀዋል፡፡
የባለፈው በጀት ዓመት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሥራ አፈጻጸም ላይ ግምገማ መከናወኑን የገለጹም ሲሆን፤ ኃላፊነታቸውን በጥሩ የተወጡትን የማጠናከር እና በሥራቸው የደከሙትን በትኩረት እንዲሰሩ አቅጣጫ የሚሰጥበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚያስችሉ የጋራ ሥራዎች ላይ መክረው የፊርማ ሥነ ስርዓት ካከናወኑት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካካል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሽ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶክተር አስራት አጸደወይን መድረኩን አስመልክቶ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ ዩኒቨርሲቲዎች በተልኳቸው አተኩረው እንዲሰሩ አስቻይ በመሆኑ የተሻለ ውጤት ማምጣት ያስችላል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በስምምነቱ ላይ የተቀመጡት የመለኪ ነጥቦች በከፍተኛ ተቋማት አቅም መነሻነት በመሆኑ፤ ለቀጣይ በትምህርት ጥራት እና መሰል ጉዳዮች ላይ የተሻለ አፈጻጸም የሚያስገኝ ነው፡፡
የሀረማያ ዩኒቨርሲቱ ፕሬዝዳትን ዶክተር ጀማል የሱፍ በበኩላቸው፤ በትናንትናው ዕለት የተከናወነው ስምምነት በትምህርት ስርዓቱ ላይ በትምህርት ጥራት እና በምርምር ዘርፍ ላይ ከፍተኛ አውንታዊ ለውጥ የሚያስገኝ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በ2018 በጀት ዓመት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በኃላፊነት እና በሙሉ አቅም በመስራት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተቀመጡ የመመዘኛ መስፈርቶችን ለመሟላት በጥረት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋና ሃጎስ ናቸው፡፡
በባለፈው በጀት ዓመት ጅማሮውን ያደረገው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት ስርዓትን ለማስተግበር የሚረዱ 5 ቁልፍ ሥራዎች አፈጻጸምን አስመልክቶ፤ በዓመቱ መጨረሻ ላይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ የተሰሩ ሥራዎች ላይ ግምገማ የሚከናወንበት አሰራር ስለመኖሩ በመድረኩ ተጠቁመዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ