ጥቅምት 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‌‎ከመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ጋር በተያያዘ በምርት ላይ የሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች፣ አምራቾችና አከፋፋዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እና በሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማከናወን በግብረ ሃይል የታገዘ ክትትል እንደሚካሄድ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ለመንግሥት ሠራተኞች በተደረገው የደመወዝ ጭማሪን ምክንያት በማድረግ የንግድ የንግድ ስርዓቱን የሚያናጋ የሰው ሰራሽ ዋጋ ጭማሪ በምርቶች ላይ እንዳይፈጠር በሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጥብቅ ቁጥጥርን እየተከናወነ እንደሚገኝ ለአሐዱ የተናገሩት የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አስፈጻሚ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ናቸው፡፡

Post image

ማንኛውም ነጋዴ ምርት አምርቶ እንደሚሸጠው ሁሉ የመንግሥት ሠራተኛ ለሚሰራው ሥራ ተጠቃሚነትን ለማስገኘት እንጂ ከንግድ ስርዓት ጋር ተያያዥነት ባለመኖሩ፤ በምርት ላይ የሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ አግባብነት እንደሌለው አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

በመሆኑም ነጋዴው ይህንን ጽንሰ ሃሳብ በአንክሮ በመረዳት ከተጠያቂነት እንዲቆጠብ አሳስበዋል፡፡

በዚህም መሠረት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተከናወነው የሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ ቁጥጥር ላይ የንግድ ስርዓቱን ማረጋጋት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም የመንግሥት ሠራተኞችን የደመወዝ ጭማሪን ምክንያት በማድረግ በምርቶች ላይ ያልተገባ እና ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የሚከናወነው ጥብቅ የቁጥጥር ሥራ ቀጣይነት እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

በተከናወነው ጥብቅ የቁጥጥር አሰራር በተጨባጭ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማራ ነጋዴ አለመገኘቱን የገለጹም ሲሆን፤ በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የደመወዝ ጭማሪን አስመልክቶ በምርቶች ላይ የሰው ሰራሽ ጭማሪ በሚያደሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ግብረ ሃይል በማቋቋም የሚካሄደው ቁጥጥር እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

Post image

በሌላ በኩል ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ የሚከሰተው ከ6 ወራት በላይ በመደርደሪያ (ሼልፍ) ላይ መቀመጥ በሚችሉ ምርቶች ላይ መሆኑን የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ገልጸዋል፡፡

አክለውም የንግድ ስርዓቱ ጤናማ እንዲሆን ለማስቻል በገበያ ላይ ያለው የምርት አቅርቦትና እጥረት መለየት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የንግድ ስርዓትን በመዘርጋት በየትኛው ምርት ላይ እጥረት እንዳለ ለመለየት ገበያ ተኮር ጥናት መከናወኑን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በዚህም የንግድ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት የገበያ ጥናት እና ቁጥጥር በትግበራ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በገበያ ጥናት እና ቁጥጥሩ ወቅት ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ የሚከሰተው ከ6 ወራት በላይ በሼልፍ ላይ መሆን በሚችሉ ምርቶች ላይ መሆኑን መገንዘብ እንደተቻለ የገለጹት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚው፤ እነርሱም የምግብ ዘይት፣ ስኳር እና መሰል ሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በንግድ ስርዓት ላይ በሕጋዊ መንገድ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ነጋዴዎች በርካቶች መሆናችን አስታውሰው፤ በአንጻሩ በሕገ-ወጥ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ ሲሳተፍ የሚገኙ መኖራቸውን እና ይህም የግብይት ስርዓቱን የሚፈትን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በ2017/18 በጀት ዓመት ከ110 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ላይ ክትትል በማከናወን ቅጣት ተጥሏል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ምርት በማምረት አቅርቦት ላይ እጥረት እንዳይከሰት በቅድሚያ በትኩረት የሚሰራበት ሂደት በመኖሩ የምርት እጥረት ሲያጋጥም ምርቱን ለነጋዴው እንዲደርስ ከመስራት አኳያም በከተማዋ የሚገኙ አምራች ማህበራት ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ